ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለጥናትና ምርምር ማካሄጃ ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ተረከበ

60

ጅማ ፣ ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለጥናትና ምርምር ማካሄጃ ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ከ12 ወረዳዎች መረከቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ገለጹ።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ዩኒቨርሲቲውን የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ የልህቀት ማእከል ለማድረግ በወረዳዎች የስነምህዳር ሁኔታ መሰረት ምርምር ይካሄዳል።

ዩኒቨርሲቲው በእጽዋትና እንሰሳት የግብርና ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ በርካታ የልማትና የምርምር ስራዎችን መከናወናቸውን ገልጸዋል።

"ዩኒቨርሲቲው በቅጥር ግቢው ውስጥ የሚሰራቸው የቡና፣ የሙዝ፣ የማንጎ፣ የንብ ማነብ እና የከብት እርባታ ስራዎች ለአካባቢው አርሶ አደሮች ጥሩ ማሳያ መሆን በመቻሉ ምርምሩን ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል" ብለዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዩኒቨርሲቲው ከወተት ሽያጭ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢማስገባቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ "የሙዝ ምርትን አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለምግብነት ማድረስ ተችሏል" ብለዋል፡፡

ከ18 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ለልምድ ልውውጥና ለተግባራዊ ልምምድ ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲው መምጣታቸውን የገለጹት ዶክተር ጴጥሮስ፤ “ይህም ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በማሳያ የልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው አርሶ አደር በቀላሉ ማምረትና መጠቀም እንደሚችል የማስተማርና የመለወጥ ተግባር እንደሚያከናውን ገልጸው፤ አሁን የተረከበውን መሬትም በስፋት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም