የሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችን ጸጥታ በመጠበቅ ለምርጫው ስኬታማነት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

210

ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችን ከፀረ-ሠላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ነፃ በማድረግ መጪው አገራዊ ምርጫ ሠላማዊና ፍትሐዊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን የሁለቱ ክልሎች የሠላምና ፀጥታ አካላት ገለፁ።

በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሠላምና ልማት ለመፍጠር በሚከናወን ቅንጅታዊ አሰራር ላይ ያተኮረ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል በህዝቦች መካከል ቅራኔዎችን በመፍጠር ለመነጣጠል ሲሰራ ቆይቷል።

“በአዋሳኝ አካባቢዎች በአስተዳደራዊ ወሰን፣ በግጦሽ መሬትና በሌሎች ምክንያቶች ግጭት በመቀስቀስ ህዝብን ከህዝብ ለማራራቅ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል” ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ ሁለቱ ክልሎች በጋራ ባከናወኗቸው ተግባራት ባለፉት ሰባት ዓመታት ተፈናቅለው የነበሩ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወት መምራት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

“አዋሳኝ አካባቢዎችን ከፀረ-ሠላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ነፃ በማድረግ ለምርጫው ሠላማዊነትና ፍትሐዊነ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ሰሞኑን በተደረገ የጋራ ክትትል ብቻ በአጎራባች ከተሞች ጥቃት ሊፈፅሙ በዝግጅት ላይ የነበሩ የአሸባሪው ሸኔ ክንፎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ሁሪሳ በበኩላቸው “የሁለቱን ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በዘላቂ ሠላምና አብሮነት እንዲሁም በልማት ለማስተሳሰር ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጅቷል” ብለዋል።

ወረዳና ቀበሌን ያጣመረ የጋራ የሠላምና ፀጥታ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የሽብር ተግባር የሚፈፅመው ሸኔ ላይ ከፌዴራል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሚወሰድበት እርምጃ እየተዳከመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህ የጠላት ኃይል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች በመዝለቅ የህዝቦችን ሠላም እንዳያናጋም ሲዳማን ጨምሮ ከሁሉም አጎራባች ክልሎች ጋር የተቀናጀ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶ ዞኑ ከሲዳማ ክልል ጋር ሰፊ የወሰን ግንኙነት እንዳለው ገልፀው፤ “ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር በጋራ በሠራነው ሥራ በርካታ ለውጦች ማምጣት ችለናል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ፀረ-ሠላም ኃይሎች በከብት ስርቆት፣ በግጦሽ መሬት ይገባኛል ሰበብ ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን በመፈፀም ቅራኔዎችን በማባባስ ተልዕኳቸውን ለማሳካት እየተራወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

“እነዚህን ግለሰቦች ከህዝቡ በመነጠል በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የጋራ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ነው ያሉት።