በምእራብ ወለጋ ዞን የአሸባሪው ሸኔን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው- ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

47

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30/2013 ( ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ሆሮ ጉድሩና አካባቢው የአሸባሪው ሸኔን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የፌዴራል ፖሊስና የዞኑ የፀጥታ መዋቅር የተቀናጀ ስራ እያከናወኑ መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፤ በዞኑ ያለው የሸኔ ቡድን ነዋሪዎችን በመግደል፣ በማፈናቀል፣ ንብረት በማውደምና በመዝረፍ አካባቢውን የሽብር ቀጠና ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

አሸባሪው ሃይል ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድና ወደ ህግ ለማቅረብ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ተሰማርተው ከአካባቢው የፀጥታ መዋቅርና ከማህበረሰቡ ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በምእራብ ወለጋ ሆሮጉድሩና አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ የማድረግ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።

በዞኑ የሚገኙ በየደረጃው ያሉ የጸጥታ ሃላፊዎች እና የፖለቲካ አመራሮች ችግሩ በአካባቢው ቀደም ብሎ የተከሰተበትን እና ማስቆም ያልተቻለበትን ምክንያት በትኩረት ማጤን ይገባቸዋልም ብለዋል።

የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ሃላፊ ሞቱማ ኮርጄ፤ በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የጸጥታ እና የፖለቲካ መዋቅሩ በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ብሔር ተኮር የሆነና ህዝብን ለማለያየትና ለማጋጨት ሆን ተብሎ የተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአካባቢው እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም