ድሬዳዋን ከመላው አገሪቱ የሚያገናኘውን አስፋልት መንገድ ከጎርፍ ጉዳት የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው

91

ሚያዝያ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ከተማን ከመላው አገሪቱ ጋር የሚያገናኘውን ዋና የአስፋልት መንገድ በጎርፍ ከመፍረስ የመታደግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የድሬዳዋ ዲስትሪክት ገለጸ።

የመንገዱ በፍጥነት መጠገን የአገሪቱን የምጣኔ ሃብትና የማህበራዊ እንቅስቃሴ መታደግ መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የፌዴራል መንገዶች ባለስልጣን የድሬዳዋ ዲስትሪክት ኃላፊ ኢንጂነር ሲሳይ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ በዋናነትም ከደንገጎ እስከ ድሬዳዋ ባለው ዋና የአስፋልት መንገድ ላይ ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

“በተለይ በሶስት ዋና ዋና የጎርፍ መውረጃዎች አስፋልቱን የመቁረጥና ከጥቅም ውጪ የማድረግ ሁኔታዎች ተከስተዋል” ብለዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የጨረታና ሌሎች ተቋራጮችን ሳይጠብቅ በራስ አቅም፣ ጉልበትና ዕውቀት ዲስትሪክቱ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት ኢንጂነር ሲሳይ።

በመንገዱ ላይ እየተገነቡ የሚገኙት የመከላከያ ግንቦች ለአስፋልቱ እንደምሰሶ የሚያገለግሉና ችግሩን የሚፈቱ ገልጸው፤ ሥራው ክረምት ከመግባቱ በፊት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።


የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር ጉልማ ታዬ በበኩላቸው መንገዱ ለድሬዳዋ ከተማ ብቻ ሣይሆን አገራዊ የትራንስፖርት መስመር መሆኑን ተናግረዋል።

መንገዱ ወደ ጂቡቲ የሚገቡና የሚወጡ የደረቅና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻዎች ድሬዳዋን ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ጋር የሚያስተሳስር በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲጠገን ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር መግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም