በክለቦች መካከል የተጫዋቾች ዝውውር እየተካሄደ ነው

80
አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በዝውውር መስኮቱ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ ይገኛሉ። የአገር ውስጥ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የተከፈተ ሲሆን የውጭ አገር ተጫዋቾች ዝውውር ደግሞ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። የዝውውር መስኮቱ መከፈትን ተከትሎ ክለቦች ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ይገኛሉ። በዚህም የደደቢት የአጥቂና የክንፍ መስመር ተጫዋች የሆነው አቤል ያለውና የጅማ አባ ጅፋር የቀኝ መስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ /አላባ/ ዛሬ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መፈረማቸውን የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምንሊክ ግርማ ለኢዜአ ገልጸዋል። ሁለቱም ተጫዋቾች በክለቡ ሁለት ዓመት ለመቆየት ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን ቡድኑ በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በሚያደርገው የቅድመ ውድድር ዝግጅት ከክለቡ ጋር ልምምድ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በዝውውር መስኮቱ ያስፈረማቸው የመጀመሪያዎቹ ተጫዋቾች መሆናቸውንም አክለዋል። በተመሳሳይ ወላይታ ዲቻ እስከ አሁን በዝውውር መስኮቱ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አምስት እንዲሁም ከከፍተኛ ሊግ ሁለት ተጫዋቾችን ማስፈረሙን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ ገልጸዋል። ክለቡ ከጅማ አባ ጅፋር ሳምሶን ቆልቻን፣  ከመከላከያ አወል አብደላን፣ ከአርባምንጭ ከተማ ፀጋዬ አበራን እና የደቡብ ፖሊስ ግብ ጠባቂን መኳንንት አሸናፊን ለሁለት ዓመት አስፈርሟል። እንዲሁም የደደቢት ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት፣ የጅማ አባ ጅፋር ሄኖክ ኢሳያስ እና የሀዲያ ሆሳዕና ሄኖክ አርፊጮንም ለአንድ ዓመት ማስፈረሙን ጠቅሰዋል። የጅማ አባጅፋር ተከላካይ አሚን ነስሩና ሌሎች ተጫዋቾች በይፋ ነገ ክለቡን እንደሚቀላቀሉ አቶ አሰፋ ገልጸዋል። ወላይታ ድቻ ክለብ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃን ውል በሁለት ዓመት ማራዘሙም የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል መከላከያ ተመስገን ገብረኪዳንን ከጅማ አባጅፋር፣ ዓለምነህ ግርማን ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና ብሩክ ቃልቦሬን ከወልዲያ ከተማ ለሁለት ዓመት ማስፈረሙን የመከላከያ ስፖርት ክለብ ተወካይ ኮሎኔል ንጉሴ አየለ ተናግረዋል። እንዲሁም ክለቡ የሐዋሳ ከተማ አምበል ፍሬው ሰለሞንን /ጣቁሩ/ ለማስፈረም ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን ተጫዋቹ ክለቡን ለመቀላቀል በቃል ደረጃ መስማማቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ክለቡ የሙሉቀን ደሳለኝ፣ ምንተስኖት ከበደ፣ ምንይሉ ወንድሙና ሽመልስ ተገኝን ኮንትራት በሁለት ዓመት ማራዘሙን አስታውቋል። ፋሲል ከተማ ከዚህ በፊት የደደቢትን ሽመክት ጉግሳ፣ ኮትዲቩዋራዊውን ከድር ኩሊባሊንና ሰለሞን ሀብቴን፣ የመቀሌ ከተማን ሀብታሙ ተከስተንና የወላይታ ድቻን በዛብህ መለዮን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው። የአገር ውስጥ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እስከ ቀጣዩ የውድድር ዓመት መጀመሪያ ድረስ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም