ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

111

ሚያዝያ 29/2013(ኢዜአ) ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ ዜጎች   ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከዳያስፖራው ከ236 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሀብት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ለሚከናወኑ ስራዎች መሰብሰቡንም ገልጿል።

መንግስት በጥቅምት ወር  "የሕወሓት ቡድን" በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችና በንጹሃን ዜጎች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ዜጎች ለችግር እየተጋለጡም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዳያስፖራው ለተቸገሩ ወገኖችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ድጋፍ ማሰባሰብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ ማቅረቡን ገልጸዋል ።

ኤጀንሲው የቀረበውን ሀሳብ ተከትሎ ፕሮጀክት በመቅረጽ ወደ ድጋፍ ማሰባሰብ ስራ መግባቱንና እስካሁን ዳያስፖራው በገንዘብና በአይነት ከ431 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

በገንዘብ ከ77 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ላይ እንዲሁም በአይነት የሕክምና መሳሪያዎች፣መድሐኒቶችና ቁሳቁሶች ከ357 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

በተለይም በአይነት ከሕክምና ግብአቶች አንጻር የጤና ሚኒስቴር ያስፈልጋሉ ብሎ የሚለያቸውን ግብአቶች መሰረት በማድረግ ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ዳያስፖራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግንና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ጠንካራ ተሳትፎ የሚያመላክት እንደሆነም አመልክተዋል።

ዳያስፖራው መንግስት በትግራይ ክልል የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ እየወጡ ያሉ ሀሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን በማጋለጥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ዳያስፖራው እየሰራ እንደሚገኝም ነው ወይዘሮ ሰላማዊት የገለጹት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በቅርቡ ላወጣው መግለጫ የዲያስፖራው ሚና ወሳኝ እንደነበርም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በ2013 ዓ.ም በጀት ዘጠኝ ወራት ዳያስፖራው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ለሚከናወኑ ስራዎች ከ236 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ  ማድረጉን ጠቁመዋል።

እስካሁን ከዳያስፖራው በአይነትና በገንዘብ ወረርሽኙን ለመከላከል ከ541 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት መሰባሰቡንም አመልክተዋል።


የአይነት ድጋፉ የጤና ሚኒስቴር በዝርዝር በለያቸው የሕክምና ቁሳቁሶች አማካኝነት ግዢ በመፈጸም ወደ አገር ውስጥ እየተላከ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከድጋፉ በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያ የሆኑ ዳያስፖራዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ  ብለዋል።


በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ምሁራን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ለመንግስት ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን እያቀረቡ እንደሆነም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቅርቡ በአሜሪካና በአውሮፓ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተደረጉ ውይይቶች ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮችና የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፍ ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት ከፍተኛ እንደሆነ መታየቱን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያን ለመጠበቅና የሚደርስባትን ያልተገባ ጫና ለመመከት እንደሚሰራ መግለጹን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ከዳያስፖራው ጋር የተደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ የሚባልና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ በዳያስፖራው ላይ ያሉ ብዥታዎችን ለማጥራት አስተዋጽኦ እንዳደረጉም አክለዋል።

በውጭ አገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎና ድጋፍ የሚያደርጉባቸው 56 የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች እንዳሉ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም