ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር ተካሄደ

71

ሚያዚያ 23/2013 (ኢዜአ) ለቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ የማጣሪያ ውድድር ተካሄደ።

የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ይህ የማጣሪያ ውድድር በሰበታ ከተማ በዛሬው እለት ተካሂዷል።

የማጣሪያ ውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች የተካሄደ ሲሆን 35 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ነው።

በወንዶች መካከል የተደረገውን ውድድር አትሌት ሹራ ቂጣታ ቀዳሚ ሆኖ አጠናቋል።

አትሌት ሌሊሳ ደሲሳ ሁለተኛ ሲሆን አትሌት ሲሳይ ለማ፣ ጫሉ ደሶ እና ክንዴ አጣነው ከሶስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ እንደየቅድም ተከተላቸው አጠናቀዋል።

በተመሳሳይ በሴቶች የ35 ኪሎ ሜትር የማጣሪያ ውድድር አትሌት ትዕግስት ግርማ ቀዳሚ ሆና ጨርሳለች።

አትሌት ብርሃኔ ዲባባ ሁለተኛ እና አትሌት ሮዛ ደረጃ ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ፈጽመዋል።

አትሌት ዘይነባ ይመር አራተኛ እና አትሌት ሩታ አጋ አምስተኛ በመሆን መርሰዋል።

ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት የቶኪዮ ኦሊምፒክ በኮቪድ-19 ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ በዚህ ዓመት የሚደረግ ሲሆን ስያሜው እንደያዘ''ቶኪዮ 2020'' በሚል የሚደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም