የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎች እየተቀዛቀዘ መጥቷል-ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

3751

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ በጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የበሽታ መከላከል ተግባራት እየተቀዛቀዙ መምጣታቸውን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ የሚካሄደው የሶስት ቀናት የጤና ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው የጤና ኤክስቴንሽን ማሻሻያ ፕሮግራምና የከተማ ጤና ንቅናቄ ለውይይት የሚቀርቡ አጀንዳዎች እንደሆኑም ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር መሰረት ዘላለም ለጉባኤው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን በቤተሰብና በማህበረሰብ ደረጃ ከማዳረስ አኳያ “እምርታዊ ለውጥ አስመዝግባለች”።

በተለይም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ለማጎልበት ሴቶችን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የራሱን ጤና ራሱ እንዲጠብቅ አስችሏል ብለዋል።

ይሁን እንጂ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በርካታ ለውጦች ማስመዝገብ ቢቻልም በአሁኑ ወቅት ፕሮግራሙ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ሚኒስቴሩ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት አረጋግጧል ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።

በዘርፉ ያሉ አመራር ለፕሮግራሙ የሚያደርጉት ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆን፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የስልጠና ጥራትና ቀጣይ የትምህርትና የሙያ ማሻሸያ እድሎች አለመመቻቸት፣ የአገልግሎት ጥራት መጓደልና የጤና ኬላዎች ምቹ አለመሆን በጥናቱ ከተገኙ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑም ተናግረዋል።

ችግሮቹን በመለየት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻልም የጤና ኬላዎችን ግብዓት በማሟላት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ ማድረግ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ብቃት ማጎልበት፣ የከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን ማጠናከር፣ አገልገሎቱን ተደራሽና ዘመናዊ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የከተማ ጤና ማጠናከር ፕሮጀክት ኃላፊ ዶክተር ህብረት ዓለሙ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በከተሞች ከሆስፒታሎች በተጨማሪ ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ጤና ጣቢያዎች ናቸው።

በተለይም የከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችንም ጨምሮ የሚሰጡት በጤና ጣቢያዎች ያሉ ሙያተኞች ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ተደራሽነታቸው አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ።

ይህም ደግሞ በጤና ጣቢያዎች ያለው የህክምና አገልግሎት ግብዓትና ፍላጎት ከተገልጋዩ ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑና ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚደረገው ድጋፍም እንዲሁ ትኩረት ማጣቱን ተከትሎ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት፣ የሃይጅንና የአካባቢ ጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑና ተደራሽ ያልሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች በብዛት መኖራቸው ለከተማ ማህበረሰብ የተለየ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ያመላክታል።

ችግሩን ለማስወገድና የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ወደ ነበረበት በመመለስ የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ለማስፋትም ችግሮቹ የተለዩ በመሆናቸው በቀጣይ መፍትሄዎቹ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም በሙከራ ከተጀመረበተ ከ1994ዓ.ም አንስቶ ከ16ሺህ በላይ ጤና ኬላዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።