ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ከምክር ቤቱ እንጠብቃለን፡- የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች

89
አሶሳ ሀምሌ 25/2010 ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ጉባኤ  የአካባቢውን ዘላቂ ሰላምና  ልማት ለማረጋገጥ  የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የመቻቻል እና የሠላም ከተማ የሆነችው አሶሳ በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህም  የክልሉ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማጓተት በልማት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ነዋሪዎቹ አስታውሰዋል፡፡ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኦልቃባ አያና  በሰጡት አስተያየት የተፈጠረው ግጭት ተወግዶ አሁን ላይ በከተማው አንጻራዊ ሠላም መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የኃይማኖት አባቶችና ሌሎችም አካላት አስተዋጽኦ  ማድረጋቸውን ጠቅሰው ዛሬ ከሚጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር የሚያግዙ ወሳኔዎች እንደሚጠብቁ ተገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩን በዘላቂነት በማስወገድ ረገድ ሊከናወኑ የሚገባቸው ቀሪ ተግባራት እንዳሉ የተናገሩት ደግሞ  ወይዘሪት ናሻ ሙክታር ናቸው፡፡ አቶ መህዲን ሼህ ኢብራሂም በበኩላቸው በአካባቢው ያሉት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን በሚገባ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው  የተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር  ከአሁን በኋላ ዳግመኛ እንዳይከሰት  የተቀናጀ ስራ ማጠናከር ይገባል፡፡ አቶ ከድር ኢሳ  የተባሉት ነዋሪ ከአሁን ቀደም በተከስተ የጸጥታ ችግር በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው ሁሉም በአንድነትና በእኩልነት ተከባብሮ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በአሶሳ ከተማ ዛሬ ከሚጀመረው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤም አሁን ያለውን ሰላም በማጠናከር ዘላቂ ደህንነትና ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም