የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የተቋቋመበት አዋጅ ሊሻሻል ነው

103

አዲስ አበባ ሚያዚያ 21/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የተቋቋመበት አዋጅ ሊሻሻል መሆኑን የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዱልቀድር ገለጹ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ የተቋሙ አብዛኞቹ ችግሮች በአዋጅ የሚፈቱ መሆናቸውን ገልጿል።

የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በተቋሙ የ10 ዓመት እቅድ በተመለከተ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር በአዳማ ምክክር አድርገዋል።

የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዱልቀድር ገልገሎ፤ የኤጀንሲውን አሰራርና የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ለማድረግ አዋጁ ማሻሻል አስፈልጓል።

በመሆኑም ኤጀንሲው ቀደም ሲል የተቋቋመበትን አዋጁን ቁጥር 553/1999 ዓ.ም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለአንድ ዓመት ያክል አዋጁን የማሻሻል ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ነው ያስረዱት። 

በአሁኑ ወቅትም አስፈላጊው ማሻሻያ ተደርጎበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን ጠቁመው ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።

አዋጁ በተለይም የኤጀንሲውን የግዥ ሥርዓቱንና የሰው ሃብት አስተዳደሩን በማዘመን ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ዳይሬክተር ጀነራሉ ገልጸዋል።

በኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባ ዮሴፍ በበኩላቸው የተቋሙ አብዛኞቹ ችግሮች በአዋጅ የሚፈቱ ናቸው ብለዋል።  

በተለይም ከግዥና ከባጀት አመዳደብ ጋር በተያያዘ ኤጀንሲው የሚያጋጥመውን የአሰራር  ችግሮች ለማቃለል አዋጁ መሻሻሉ ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ገልጸዋል።  

የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲልክው ምክር ቤቱ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲወያይበትና እንዲያጸድቀው ቋሚ ኮሚቴው ይሰራል ነው ያሉት።  

በሌላ በኩል ኤጀንሲው ኮቪድ 19 ወረርሺኝን ለመከላከል በሚደረገው ብሔራዊ ጥረት የመከላከያ ግብዓቶችን በማሰራጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል።

ኤጀንሲው የጸጥታ ችግር በተከሰተባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች የተለያዩ መድሃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦቶች እንዳይስተጓጎሉ መሥራቱን አድንቀዋል።

ያም ሆኖ መድሃኒቶችን በፍጥነት በማድረሰ በኩል ያሉበትን ውስንነቶች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት መፍታት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።

ኤጀንሲው ባስተዋወቀው የ10 ዓመቱ እቅድ ውስጥ ከአገር ውስጥ የሚመረተውን መድሃኒት ከ20 በመቶ ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ይዟል።

በተጓዳኝም የመድሃኒት አቅርቦት ሠንሰለቱን ከአምራች እስከ ተጠቃሚ ድረስ ያለውን አሰራር በቴክኖሎጂ ለማዘመንም እቅድ አውጥቷል።  

እነዚህን ጨምሮ ኤጀንሲው 15 ፕሮጀክቶችን በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ይዟል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም