የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
ስትራቴጂክ እቅዱ በኢትዮጵያ ያለውን ዝቅተኛ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የሚያሻሽል ነው ተብሏል።
ኤጀንሲው ሁሉም ዜጎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማከናወን እንዲችሉ የሚያግዝ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስሩ የወሳኝ ኩነቶች ተብለው ከተለዩት ውስጥ የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻና ፍቺ የምዝገባ ሂደቶች ናቸው።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በኢትዮጵያ ልደት 20 ነጥብ 4 በመቶ፣ ሞት 10 ነጥብ 3 በመቶ፣ ጋብቻ 8 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም የፍቺ ምዝገባ 5 ነጥብ 1 በመቶ ብቻ ሆኖ ዝቅተኛ ምዝገባ ከሚከናወንባቸው አምስት የአፍሪካ አገራት መካከል ትገኛለች።
በመሆኑም ከ2014 እስከ 2018 ዓ.ም በተዘጋጀው ስትራቴጂክ ፕላን መሰረት ከአምስት ዓመት በኋላ የልደትን ምዝገባ 80 በመቶ፤ ሞት 50 በመቶ፣ ጋብቻ 50 በመቶ፣ እንዲሁም ፍቺን 40 በመቶ ለማድረግ ታቅዷል።
የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል እንዳሉት በአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ዜጎች ስለወሳኝ ኩነት በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው በራሳቸው ተነሳሽነት እንዲመዘገቡ ማድረግ ነው።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች የአደረጃጀት እንዲሁም የሂደት ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ይሄንን በማሻሻል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
የሀገሪቱም ጥቅል እቅድ ለማዘጋጀት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ገልጸዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
ስትራቴጂክ ዕቅዱ አንድ ዓመት የፈጀ ጥናት የተደረገበት መሆኑን ገልጸው፤ የህግና ፖሊሲ እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን ጥምረት ከሚያስፈልገው በጀት ጋር አጣምሮ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
"ሁሉም የሚታወቅባት ኢትዮጵያ እንዲትኖር እንፈልጋለን" በሚል እሳቤ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ሙጂብ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚያወጣቸው መረጃዎች በናሙና ሳይሆን እኛ በምንሰጠው የተመዘገበ መረጃ እንዲሆን እናደርጋለን ብለዋል።
መንግስት ትምህርት ቤት ለመክፈት ጤና ጣቢያ ለመገንባት ወይም ሌላ አስፈላጊ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችል አሰራር ነው ብለዋል።
የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የምርምርና አሰራረ ስርዓት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ መኮንን፤ የመንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነትና በሀገሪቱ ያለው ያልተማከለ አስተዳደር ዕቅዱን እውን ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ስትራቴጂክ እቅዱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ተጠቃሚ የሚሆንበት መረጃ ለመንግስት ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሀገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመንደፍ ጉልህ ሚና ስላለው ዜጎችም ይህንኑ ተገንዝበው እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።