ቀጥታ፡

በሀገሪቱ 5 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 5ተኛው ዙር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሀ ግብር ተጀመረ- ሚኒስቴሩ

ድሬዳዋ፣ሚያዚያ 17/2013 /ኢዜአ/ በመላው ሀገሪቱ 5 ሚሊዮን የገጠር የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 5ተኛው ዙር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ይህን ያስታወቁት ዛሬ ድሬዳዋ ተገኝተው የልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር በሐረሪ ክልልና በድሬዳዋ አስተዳደር በይፋ ባስጀመሩበት ስነ ስርአት ላይ ነው፡፡

"መርሃ ግብሩ ሥር የሰደደ የምግብ ችግር በማቃለል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡

"መርሀ ግብሩ የምግብ ክፍተትን በመድፈን ጥሪት ለማፍራት ያስችላል" ያሉት ወይዘሮ አይናለም በ4ተኛው ዙር ለ5 ዓመታት የተከናወኑ የልማታዊ ሴፍትኔት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች መልካም ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ምንጭ የማጎልበት፣ መንደርን ከመንደር የሚያገናኙ የመንገድና መሰል የመሠረተ-ልማቶች ግንባታና የሥርዓተ -ምግብ ማሻሻል ስራዎች ለግብርናው ልማት ወሳኝ አበርክቶ እንደነበራቸው ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ለመገንባት ለሚከናወኑ ስራዎች መደላደል የፈጠረ ስራ መከናወኑን ወይዘሮ አይናለም አስታውቀዋል።

"በ5ተኛው ዙር የቀደመውን ተሞክሮ ይበልጥ በማጠናከር በስምንት ክልሎችና በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የምግብ ዋስትናን ያላረጋገጡ የገጠር ነዋሪዎች የአደጋ ተጋላጭነትን በመቀነስ ኑሯቸው እንዲሻሻል ይደረጋል" ብለዋል።

መርሃ ግብሩ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሲዳማ፣ በአፋርና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር እንደሚተገበር ወይዘሮ አይናለም አስታውቀዋል ።

መርሃ ግብሩ ይፋ በተደረገበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሣተፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር "በድሬዳዋ አስተዳደር መርሃ ግብሩ ከተጀመረ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ከ64 ሺህ 700 በላይ ችግረኛ የገጠር ነዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል" ብለዋል፡፡

በጤና፣ በትምህርት፣በመስኖ ልማት ሥራዎች ተሰማርተው ኑሯቸውን በማሻሻል ከሚገኙት በተጨማሪ በዕድሜና በጤና ሣቢያ አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ እየተደገፉ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

ላለፉት አራት የመርሃ ግብሩ ምዕራፎች ከ10 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመርሃ ግብሩ ተመርቀው በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ወደ ማረጋገጥ ተግባራት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

5ተኛው ዙር ልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር ይፋ በተደረገበት ስነ ስርአት ላይ በፌደራል ስራ ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የምግብ ዋስትና ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ደምሴን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም