ቀጥታ፡

የዋግ ልማት ማህበር ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ሰቆጣ፣  ሚያዝያ 17/2013 ( ኢዜአ ) የዋግ ልማት ማህበር በብሄረሰብ አስተዳደሩ በቅርቡ በተከሰተ የፀጥታ ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የ1 ሚለዬን ብር ድጋፍ ማድረጉን የብሄረሰብ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በሪሁን ኪዳነ ማርያም በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የትህነግ ጁንታ ወደ ብሄረሰብ አስተዳደሩ በመግባት ተደጋጋሚ ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል።

በኮረምና ራያ ሾልኮ ሊያመልጥ የነበረው የትህነግ ጁንታ በደረሰበት ከፍተኛ ምት የተበተነው ሃይል ወደ ፃግብጅ ወረዳ ዘልቆ በመግባት በንፁሃን ዜጎች፣ በሚሊሻና በፓሊስ አባላት ላይ ጥቃት ማድረሱን አውስተዋል።

በጥቃቱ መስዕዋት ለሆኑ የንጸሁን ዜጎች፣ የሚሊሻና የፖሊስ ቤተሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የዝቋላ ፣ ሰቆጣ ዙሪያ ፣ ፃግብጅ ወረዳና የሰቆጣ ከተማ አስተዳደሮች በምክር ቤቶች ማስወሰናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተጎጂ ቤተሰቦች የደረሰባቸውን ችግር ለማቃለል የዋግ ልማት ማህበር እያደረገ ያለውን ጥረት በማመስገን ሌሎች አካላትም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አምላኩ አበበ በበኩላቸው ማህበሩ በብሄረሰቡ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ  የ1ሚሊዬን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

"የልማት ማህበሩ  የገንዘብ ድጋፍ ለ71 የተጎጅ ቤተሰቦች በነፍስ ወከፍ ከ14 ሽህ ብር በላይ በማከፋፈል የኑሮ ጫናቸውን ለማቃለል የተደረገ   ነው" ብለዋል።

ድጋፉን ቀጣይነት ያለው ለማድረግ  በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የልማት ማህበሩ አባላትና ደጋፊዎችን የማስተባበር ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው የተጎጅ ቤተሰቦች መካከል አስር አለቃ ተፈራ መኮንን እንዳሉት በልማት ማህበሩ የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ የተፈጠረባቸውን የኑሮ ጫና የሚያቃልልላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል ቃል የተገቡ ድጋፎችን ተግባራዊ በማድረግ ለህዝባቸው ሰላምና ደህንነት መጠበቅ መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖችን ማክበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

መልአከ ብርሃን ነብዩ ልዑል ዳዊት በበኩላቸው "ልማት ማህበሩ ያደረገው ድጋፍ ለብሄረሰብ አስተዳደሩ ህዝብ አለኝታነቱን ያሳየበት ነው "ብለዋል።

አሁን ላይ የዞኑ የጸጥታ አካላት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና የመከላከያ ሰራዊት ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት አካባቢው ቀድሞ ወደ ነበረበት ሰላም መመለሱን ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም