ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማበልጸግ እየሰራሁ ነው- ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ

118

ዲላ፣  ሚያዚያ 17/2013 (ኢዜአ) ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማበልጸግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ቀን የተካሄደ የጉጂ ኦሮሞ የጥናት ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማበልጸግ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም የገዳ ስርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ኢንስቲትዩት ከፍቶ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ባለፈ ከ700 የሚበልጡ ተማሪዎችን በገዳ ስርዓት ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ድረስ እያስተማረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የገዳ ስርዓት ለዘመናት ሳይሸራረፍ በሚተገበርበት የጉጂ ዞኖች አካባቢ ዩኒቨርሲቲው መገኘቱ በዘርፉ ለሚከናወኑ ጥናቶች በቅርበት መረጃ ለማግኘት አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገር በቀል እውቀትን ከማበልጸግ ባለፈ በሳይንስ የተደገፈ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ለውጥ ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የገዳ ስርዓት ኢንስቲትዩት ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ ጉዬ በበኩላቸው በገዳ ስርዓት ዙሪያ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።

የማህበረሰቡን ባህልና ወግ ሊያሳድጉ የሚችሉ መፅሃፍት በመምህራን ተዘጋጅተው እንዲታተሙ ድጋፍ በማድረግ ለንባብ መብቃታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማሳደግ በትጋት እየሰራን ነው" ያሉት ሃላፊው በተለይ ለሰላምና ለወንድማማችነት ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችን በምርምር በማዳበር ወጣቱ ትውልድ እንዲማርባቸው እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በፎረሙ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የዩኒቨርሲቲውን አመራሮች ጨምሮ አባ ገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም