በጋምቤላ በውሀ አካላት ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ህዝቡ በጋራ እንዲከላከል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ በውሀ አካላት ላይ የተከሰተውን እንቦጭ ህዝቡ በጋራ እንዲከላከል ተጠየቀ
ጋምቤላ፣ ሚያዝያ 17/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የእምቦጭ አረም በውሃ አካላት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ህዝቡ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ።
በክልሉ በሀይቆችና ኩሬዎች ላይ የተከሰተ እንቦጭ አረም የመስኖ ውሀን እያደረቀና የአሳ ሀብትን እያጠፋ መሆኑ ተመላክቷል።
‘‘የተፈጥሮ ሐብታችን በመጠበቅ ብልጽግናችን እናረጋግጣለን ’’ በሚል መሪ ሃሳብ የእምቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ ትላንት በኢታንግ ልዩ ወረዳ ተጀምሯል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በወቅቱ እንዳሉት የእምቦጭ አረም በአማራ ክልል ጣና ሐይቅ ሲሰማ የነበረው ችግር በጋምቤላ ክልልም መታየቱ የሚያስደነግጥ ጉዳይ ነው ።
አረሙ በተለይም በኩሬዎች፣ በሐይቆችና ሌሎች ሰፊ የውሃ አካላት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ሁኔታው ለመስኖና በዓሳ ሀብት ላይ ጭምር ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
አረሙ በበለጠ ከመስፋፋቱ በፊት መላው የክልሉ ህዝብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለመከላከል ጥረት እንዲያደረጉ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት አረሙን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑም አስገንዝበዋል።
በዕለቱ የተጀመረው ዘመቻ ዓላማ ማህበረሰቡ በሚጠቀምባቸው ሐይቆች፣ ኩሬዎችና ሌሎች የውሃ አካላት በአረሙ የተጋረጠውን አደጋ በህዝባዊ ተሳትፎ ለመከላከል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኮይት ሉዑል የእምቦጭ አረም በኩሬዎች፣በሐይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት እያደረሰ ባለው ችግር አርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ ሲያገኘው የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በእለቱ በአራት ሄክታር የኩሬ ውሀ ላይ የተከሰተን የእምቦጭ አረም የማጽዳት ስራ መካሄዱን አክለዋል ።
ኩሬው ቀደም ሲል የአካባቢው ነዋሪዎች በበጋ ወራት ውሃና ዓሳ ፍለጋ ወደ ባሮ ወንዝ ሲያደርጉ የነበረውን ጉዞ ያስቀረ እንደነበር ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ እምቦጭ አረም በኩሬ ውሃው ላይ አደጋ መደቀኑን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው በዕለቱ እየተጸዳ ያለውን ጨምሮ በሌሎች ኩሬዎች ላይ አረሙ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዘመቻ ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኮቶ ቶክ በሰጡት አስተያየት በኩሬው ላይ የእምቦጭ አረም በመከሰቱ ቀደም ሲል ሲያገኙት የነበረው የዓሳ ምርት በእጀጉ መቀነሱን ተናግረዋል።
ሁኔታውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የኩሬው ውሃ እንዳይጠፋባቸው የማጽዳት ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከአስር ዓመት በፊት ከመንገድ ስራ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ኩሬ በበጋ ወራት ለከብቶቻቸው ውሃ ፍለጋ ወደ ባሮ ወንዝ ያደርጉት የነበረውን እንግልት አስቀርቶላቸው እንደነበር የገለጹት ደግሞ የባዴል ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ቶች ጋች ናቸው።
አረሙን ለማስወገድ ለጀመሩት ስራ መቃናት የመንግስት ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።
በመረሃ ግብሩ ላይ ነዋሪዎቹ በኩሬው የዓሳ ሀብት መኖሩን ለማመላከት የዓሳ ምርት ያቀረቡ ሲሆን እንቦጭ የማስወገድ ዘመቻው ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ ተመላክቷል።