በአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቋመ
ባህር ዳር፣ ሚያዚያ 17/2013 (ኢዜአ ) በ6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በአማራ ክልል የሚወዳደሩ ዘጠኝ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አቋቋሙ።
በምርጫው ሂደት ፓርቲዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ምርጫው ሰላማዊና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ምክር ቤቱ መቋቋሙ ተመልክቷል።
የጋራ ምክር ቤቱን ትናንት የመሰረቱት የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራት ህብረት፣ ኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ ብልፅጽግና ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሃይሎች ንቅናቄና እናት ፓርቲ ናቸው።
የእናት ፓርቲ የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ጀምበሩ አለማየሁ ለኢዜአ እንደገለፁት የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት የምርጫ ሂደቶች የተሻለ ሁኔታ ይስተዋልበታል።
በሃገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ መቃወም ላይ መሰረት ካደረገ እንቅስቃሴ በመላቀቅ ተፎካካሪ ሆኖ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ መቋቋም እርስ በእርስ ተቀራርቦ በመስራት በእንቅስቃሴ ሂደት ችግር እንዳይፈጠር ቢፈጠርም በሰከነ አግባብ በመወያየት ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
"እንዲሁም እርስ በእርስ ከመጠራጠር፣ ከመጠላለፍና ጥል ከመፍጠር በመላቀቅ የሰለጠነ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲፈጠርም ያግዛል" ብለዋል።
ከሁሉም በላይ በዚህ ምርጫ አሸናፊው ህዝብ እንዲሆን እንዲሁም ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት በማጎልበት ምክር ቤቱ የጎላ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።
የአማራ ዴሞክራሲ ንቅናቄ (አዴሃን) ሊቀመንበርና የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው አሁን ያለው የፖለቲካ ድባብ ምርጫው የተሻለ ተስፋ እንዲጣልበት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ምርጫው ከምንም በፊት የህዝቡ ሰላም ተጠብቆለት መከናወን እንዳለበት ጠቁመው ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰለጠነ አግባብ መንቀሳቀሳቸው ለምርጫው ውጤታማነት ድርሻው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።
የምከር ቤቱ መቋቋም ለምርጫው ፍትሃዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርስ ተቀራርቦና ተደጋግፎ መስራት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።
"የጋራ ምክር ቤቱ መቋቋም በምርጫ ሂደት የሚገጥሙ ችግሮችን በመለየትና ተቀራርቦ በመነጋገር ከስር ከስሩ እልባት በመስጠት ጥቃቅን ችግሮች እንዳይሰፉ ለማድረግ የተሻለ እድል ይሰጣል" ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ይስተዋል እንደነበረው አይነት ከጫፍና ጫፍ ሆኖ መጓተት፣ ቅሬታና አቤቱታ ማብዛት እንዳይኖርና ምርጫው በህግና ህግ አግባብ እንዲከናወን እንደሚያግዝ አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ በተገባው ቃል ኪዳን መሰረት ህግን መሰረት አድርጎ በመስራት ምርጫው በሰላማዊና ተዓማኒነት ባተረፈ አግባብ እንዲከናወን አጥብቆ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
''የጋራ ምክር ቤቱ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ሊፈጠሩ የሚችሉ እንከኖችን ፈጥኖ ለማስተካከል ላቅ ያለ ሚና ያበረክታል'' ያሉት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል የፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ ናቸው።
"ብልፅግና እንደ ፓርቲም ሆነ እንደገዥ መንግስት ምርጫው ያለምንም እንከን በሰላማዊ መንገድ ሁሉንም ባሳተፈ አግባብ እንዲከናወን ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች በእጅጉ በተሻለ አግባብ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል" ብለዋል።
የምርጫ ቦርድ የሚያቋቁመው ምክር ቤት በመዘግየቱ ምክንያት በየአካባቢው ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አደረጃጀት በመፍጠር በጋራ እንዲሰሩ በማድረግ ቀደም ሲል ስራው መጀመሩን ገልፀዋል።
"አሁን ላይ ደግሞ በክልሉ ለምርጫ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መቋቋሙ ለምርጫው እንቅፋት የሚሆን ችግር እንዳይፈጠር ተነጋግሮና ተግባብቶ ለመስራት ያስችላል" ሲሉ ተናግረዋል።
ችግር ቢፈጠር እንኳ ከመስፋቱና ወደ ሌላ አቅጣጫ ከመሄዱ በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ በመመካከር ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
"ዛሬ በጋራ ምክር ቤቱ ምስረታ የነበረው የውይይት አውድ ከድሮው የተለየና በጠላትነት ከመተያየት ወጥቶ በወንድማማችነት በመግባባት ስራዎችን መስራት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው" ብለዋል።
ፓርቲው የጋራ ምክር ቤቱን ደንብ አክብሮ በመንቀሳቀስ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መኳንንት መከተ እንዳሉት በክልሉ ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በርከት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድሩ እጩዎችን አቅርበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ምርጫው ያለምንም ችግር እንዲከናወን እርስ በእርስ በመነጋገርና ችግሮቻቸውን በመፍታት ለምርጫው ተዓማኒነት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የተቋቋመው ምክር ቤት ከዚህ በፊት በፓርቲዎች መካከል ይስተዋል የነበረውን ሩቅ በሩቅ ሆኖ የመወቃቀስ፣ ባልተጨበጠ መረጃ የመካሰስ ልምድ በመተው ተቻችሎ የመወያየትና የመተጋገዝ ባህል እንዲሰፋ እድል የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ፓርቲዎቹ ችግሮችን ቀድሞ በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫ እያስቀመጡ 6ኛው ሀገራዊና ክልል አቀፍ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን እንደሚረዳ ጠቁመው ምርጫ ቦርድም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በቀጣይም በዞንና በወረዳ ደረጃ ምክር ቤቱን ለማቋቋም ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመው ዛሬ በምስረታ መርሃ ግብሩ ያልተገኙ ፓርቲዎችም በቀጣይ ፍላጎቱ ካላቸው የሚካተቱ እንደሆኑ ሀላፊው አመላክተዋል።
ፓርቲዎቹ በምክር ቤቱ በቀጣይ የአሰራር ድንብ ላይ በመወያየት የተፈራረሙ ሲሆን በመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀምና የኦዲት ቁጥጥር ኮሚቴ በማቋቋም ስራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።