ቀጥታ፡

የዘንድሮው ምርጫ የሕዝቦችን ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ በማስገባት ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት መመሥረት ያስችላል -- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17 /2013 (ኢዜአ) የዘንድሮው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የሕዝቦችን ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ ማስገባቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የሕዝብን ጥያቄዎች “ከጎዳና ወደ ፓርላማ” የሚወስድ ምርጫ በሚል ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በሚመለከት መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫቸው “የዘንድሮው ምርጫ የዘመናት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ቁልፍ እንደሆነ መዘንጋት ሞኝነት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በሀገራችን ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ጥያቄ ወደ ተገቢው የዴሞክራሲ ባሕል መንገድ ማስገባት አልተቻለም ነበር ብለዋል።

ጉዳዩን ወደኋላ አርዝመን ካየነው ምናልባትም ከታኅሳሱ ግርግርና ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የሕዝባችን የፖለቲካ ጥያቄዎች በዋናነት የሚንጸባረቁት አንድም በጎዳና ላይ ዐመጽ፣ ሁለትም በጦር መሣሪያ አማካኝነት ነበር በማለትም አስታውሰዋል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የሕዝብን ጥያቄዎች “ከጎዳና ወደ ፓርላማ” የሚወስደው የዘንድሮው ምርጫ የዘመናት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ቁልፍ እንደሆነ መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡

በሀገራችን ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ጥያቄ ወደ ተገቢው የዴሞክራሲ ባሕል መንገድ ማስገባት አልተቻለም ነበር።ጉዳዩን ወደኋላ አርዝመን ካየነው ምናልባትም ከታኅሳሱ ግርግርና ከተማሪዎችእንቅስቃሴ ጀምሮ የሕዝባችን የፖለቲካ ጥያቄዎች በዋናነት የሚንጸባረቁት አንድም በጎዳና ላይ ዐመጽ፣ሁለትም በጦር መሣሪያ አማካኝነት ነበር። ሁለቱም መንገዶች እጅግ ኋላቀርና አውዳሚዎች እንደነበሩ እስኪበቃን አይተናል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ በድኻ ወገቧ አስተምራ ለከፍተኛ ደረጃ ያደረሰቻቸውአያሌ ተማሪዎች እና ምሁራን በገፍ አልቀውበታል።ለዓመታት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች በቀናትልዩነት ወደ ትቢያነት ተለውጠዋል። እንዲያም ሆኖ የዘመናት ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ አላገኙም።

ለምን?በአንድ በኩል ነጻ አውጭ ድርጅቶች፣ ጠብመንጃ አንሥተው በገቡበት ጫካ "ራስን በራስ የማስተዳደርየብሔሮች መብት ዛሬውኑ ይከበር" ሲሉ፤ በሌላ በኩል የከተማ ሽምቅ ውጊያ የጀመሩ ኃይሎች "ሕዝባዊመንግሥት ዛሬውኑ" እያሉ ሲፋለሙ ነበር።

ከፍልሚያው በኋላ፣ የጭቆና ቀንበር ጫነ የተባለውድርጅት ከመንበረ ሥልጣኑ ሲገለል፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቅርጥፍ አድርገው የበሉጥያቄዎች በወጉ መልስ ሳይቸራቸው፣ “የሞግዚት አስተዳደር” እንዲያበቃ ዳግም ወደ ጫካ፣ ዳግምወደ ጎዳና ተወጥቷል።

ለምን?“ምርጫ 97” የሕዝብን ጥያቄ ወደ ካርድ ማምጣት የቻለ ቢሆንም፣ ሂደቱ በአግባቡ ባለመቋጨቱምክንያት ውጤቱ የድሮው ዓይነት የጎዳና ዐመጽና የበረሃ ትግልን ወልዷል።

በጎረቤት ሀገራትተደብቀው ኢሕአዴግን በጦር መሣሪያ ለመጣል ሲታገሉ የነበሩት ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምንጩ ያንንወርቃማ ዕድል በአግባቡ ባለመጠቀም የተፈጠረ እንደሆነ አይካድም።

መቀመጫቸውን አሜሪካናአውሮፓ ያደረጉ፣ በሳይበርና በሜንስትሪም ሚዲያዎች ታግዘው ሲከናወኑ የነበሩ የአክቲቪዝምእንቅስቃሴዎች በሀገር ውስጥ ካሉ የተቃውሞ ኃይሎች ጋር በመጣመር ዜጎች ድምፃቸውን በየጎዳናውእንዲያሰሙ በመገፋፋታቸው፣ ለብዙዎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።

ለምን?የእነዚህ ሁሉ “ለምን” ጥያቄዎች መልሱ የሚያጠነጥነው የሕዝብ ድምፆች ተገቢውን ቦታ አግኝተውመሰማት አለመቻላቸው ነው።በሌላ አማርኛ ፓርላማችን እውነተኛ ፓርላማ የሚያደርገውን ባህሪእንዲላበስ ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት የተፈጠረ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ልዩ ልዩ የሕዝብ ድምፆችየሚሰሙበት ፓርላማ ኖሯት አያውቅም።ሕዝብ ድምፁ በፓርላማ የሚሰማለት ከሆነ በምን ምክንያትሕይወቱ በየጎዳናው ወይም በየዱር ገደሉ እንዲቀጠፍ ይፈልጋል? በምንም፡፡በዓለማችን ላይ በዴሞክራሲ ከፍ አድርገን የምንጠቅሳቸው ሀገራት የሕዝብ ጥያቄዎች የሚደመጡትበየጎዳናውና ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ሳይሆን በምክር ቤቶቻችው ነው።

ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጁውሳኔዎች ሁሉ የሚወሰኑት በምክር ቤቶቹ አማካኝነት እንጂ በሌላ አካል አይደለም። ውሳኔውምበሀገሬው ሕዝብ ሙሉ ተቀባይነት አለው፡፡ይሄንን ያደረገው ወደ ውሳኔው ያደረሱት ሐሳቦች የእውነትየሕዝብን ፍላጎት የሚያንጸባርቁ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ሂደቱ አሳማኝ ስለሚሆን ጭምር ነው።

ለዚህም ሕዝቡና መንግሥት ያልተጭበረበረና የዜጎችን ድምፅ በትክክሉ የሚገልጽ ምርጫ እንዲካሄድ ከምንም በላይ የተለየ ትኩረት ሰጥተው ይሠራሉ። በዚህ መልኩ አንዴ ምርጫው የተሳካ ሆኖከተከናወነ ሕዝቦች ወደ ጎዳና መውጣት ሳያስፈልጋቸው በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድምፃቸው ስለ ሚሰማላቸው፣ ዜጎቻቸው ሰፊ ጊዜያቸውን በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ አውለው፣ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማሳደግ ይጠቀሙበታል።

የዘንድሮው የሀገራችን ምርጫ ለኢትዮጵያውያን ይሄንን ወርቃማ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ በተሳካመልኩ ማከናወን ከቻልን በእርግጥም የሕዝባችንን ድምፅ ከጎዳና ወደ ፓርላማ፣ ከጫካ ወደ ጠረጴዛዙሪያ ይመልሳል፡፡ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በተሳካ መልኩ ማከናወን ቢቻል፣መንግሥት የመመሥረቻ የሚያስችል መቀመጫ (ሃምሳ ሲደመር አንድ) ካገኘው ፓርቲ ባለፈ ሌሎችፓርቲዎች ቁጥራቸው የማይናቅ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያገኛሉ።

ይህ ማለት ለኢትዮጵያዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ ማለት ነው።2የሀገርን እጣ ፈንታ የሚወስኑ ውሳኔዎች በጥቂት ግለሰቦች/ቡድኖች የሐሳብ የበላይነት ተፈጻሚመሆናቸው አብቅቶ ብዙ ድምጾች ተሰምተው፣ ብዙ ክርክሮች ተደርገው፣ ብዙ ሐሳቦች ተሰጥተውበትይወሰናል፡፡

ለዚህ መሳካት የምርጫው ሂደት ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያስነሱ የሚያስችሉ ጉዳዮችላይ ርምጃዎች ቀድመው ተወስደዋል። ከየትኛውም ፓርቲ ፍላጎት ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድበታሪካችን የመጀመሪያው አሁን ያለው የምርጫ ቦርድ እንደሆነ ሁላችንንም ያስማማል የሚል ግምትአለኝ።

ያም ሆኖ፣ ሁላችንም ካርድ ወስደን ፍቃዳችንን ሊሞላልን የሚችለውን ተወካይ እስካልመረጥንድረስ የተሠራው ሁሉ ትርጉም የለሽ ይሆናል፡፡ሀገራችንም የኖረችበት አዙሪት ውስጥ ትወድቃለች፡፡ስለዚህ የዕለት ተዕለት ችግርን በዕለት ተዕለት መፍትሔ ከመጋተር፤ ዋናውን መሠረታዊ ችግርበመሠረታዊ መፍትሔ ማስወገድ አዋጭ ነው።

አንዳንዶች ምርጫውን በዚህ ሰዓት ማድረግ ቅንጦት እንደሆነ አድርገው የተለያዩ ምክንያቶችንያስቀምጣሉ። በማንነታቸው ሰዎች እየተገደሉና እየተፈናቀሉ፣ በተለያዩ አቅጣጫዎች ሽምቅ ተዋጊዎችሰላማዊውን ሕዝብ ረፍት እየነሡት ስለ ምርጫ መጨነቅ ተገቢ አይደለም ይላሉ።

ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ ጥቃቶች ከውጭ ሀገራት እየተሰነዘሩብን፣ በዚህ በኩል የኑሮ ውድነትናየኮሮና ወረርሽኝ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ አደጋ እየጋረጠብን፣ ሌላ ራስ ምታት የሚሆን፣ ተጨማሪቀውሶችን ሊጋብዝ የሚችል ምርጫ ማድረግ እብደት እንደሆነ ይገልጻሉ።

እነዚህ ምክንያቶች ከላይ ከላይ ሲታዩ አሳማኝና የሰዎችን ልብ የሚገዙ ቢመስሉም፣ ከላይ በሰፈሩትመነጽሮች ሲፈተሹ ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ መከራከሪያዎቹ በሀገራችን የሕዝብቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ለውጭ ሀገራት ኃይሎችእና የግል ፍላጎታቸውን ለሚያሳድዱ የውስጥ ኃይሎች ካልሆነ በቀር ደካማ መንግሥት ስለኖረን ሀገራችን ምንም ነገር እንደማታተርፍ ግልጽ ነው፡፡

ሁላችንም በንቃት በምንሳተፍበት የዘንድሮውምርጫ የሕዝቦች ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ መግባቱ እንዳለ ሆኖ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለውመንግሥት መመሥረት በመቻሉ ሀገራችን የምታገኘው ጥቅም ከላይ ለቀረበው መከራከሪያ በቂ መልስመሆን ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!! ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዚያ 17፣ 2013

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም