ሴቶች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ከወዲሁ ተመዝግበው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር ከወዲሁ ተመዝግበው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ጥሪ ቀረበ
ፍቼ ሚያዝያ 16/2ዐ13 (ኢዜአ) ሴቶች መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በቅርቡ በሚካሄደው ስድስተኛ ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ከወዲሁ ተመዝግበው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶች ማህበር ጥሪ አቀረበ፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዘሮ ይርገዱ አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሴቶችን ችግርና ጥያቄዎቻቸው መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉት ሴቶች እራሳቸውን በምርጫው በመመዝገብ ሌሎች እንዲመዘገቡ በማበረታታት ሊሆን ይገባል፡፡
ሴቶች በምርጫው እስከ ድምጽ መስጫው እለት በንቃት ተሳትፈው መብትና ጥቅማቸውን በትክክል የሚያስከብርላቸውን ወኪል ለመምረጥ ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ለዚህም በቀሪዎቹ ቀናት በመመዝገብ የምርጫ ካርድ በየአቅራቢያቸው በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በመመዝገብ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማህበሩ ከዞን እስከ ቀበሌ ባሉት ቅርንጫፎቹ አማካኝነት ሴቶች በመራጭነት እንዲሳተፉ የተጠናከረ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ በዘንድሮ ምርጫ ከቀድሞ ይበልጥ የዞኑ ሴቶች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሴቶች በእጩ ተወዳዳሪነት፣ በመራጭነትና በታዛቢነት እንዲሳተፉ በማህበሩ 15ዐሺህ አባላት በኩል የተለያዩ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከማህበሩ አባላት መካከል ወይዘሮ ጠጂቱ አዱኛ በሰጡት አስተያየት ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም የሚፈልጉትን ዕጩ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች ሴቶች በመራጭነት በስፋት ቢሳተፉ ትክክለኛና የሚበጃቸውን ከወዲሁ ለይተው ለመምረጥ እድል ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
የፍቼ ከተማ የቀበሌ አራት ነዋሪ ወይዘሪት ምስራቅ ዴክሲሳ በበኩሏ የመራጭነት ካርድ አስቀድማ እንደወሰደች ጠቁማ ሌሎች ሴቶች ጨምሮ ሁሉም ዜጎች የመራጭነት ካርድ በመውሰድ በመብታቸው እንዲጠቀሙ መልዕክት አስተላልፋለች፡፡