'ፀኃይ' የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር የተሰኘ መጽሃፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
'ፀኃይ' የኢትዮጵያ አቪዬሽን አጀማመር የተሰኘ መጽሃፍ ተመረቀ
ሚያዚያ 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ታሪክ ላይ ትኩረት ያደረገ "ፀኃይ' የኢትዮጵያ አቬይሽን አጀማመር" የተሰኘ መጽሃፍ ዛሬ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተመረቀ።
መጽሃፉ ከ1921 እስከ 1928 ዓ.ም ባሉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የአውሮፕላን በረራ አገልግሎት እንዴት እንደተጀመረና እንደተስፋፋ ይዳስሳል።
የአውሮፕላን በረራ ትምህርት ቤት እንዴት እንደተጀመረ፣ የወቅቱ የውጭ አገራት በረራዎችና ያጋጠሙ የዘርፉ ችግሮችንም መጽሃፉ በስፋት ዳስሷል።
የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች በሁለተኛው የኢጣሊያ ጦርነት ወቅት የነበራቸው ሚናና ስለቀድሞዎቹ አብራሪዎች ህይወትም መጽሃፉ ትኩረት አድርጓል።
በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1928 ዓ.ም ስለሰራችውና ጸሃይ ተብላ ስለተሰየመችው አውሮፕላን መጽሃፉ ሰፊ ማብረሪያ ይዟል።
የመጽሃፉ ደራሲ ካፒቴን ዘለዓለም አንዳርጌ እንደገለጹት፤ መጽሃፉን የተለያዩ መረጃዎችን በማጣቀስና በማመሳከር ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ጸሃይ ስለተባለችው አውሮፕላን በጣሊያኖች እንዴት እንደተወሰደችና አሁን በምን መልኩ እንደምትገኝ መጽሃፉ በስፋት ማተቱን ጠቁመዋል።
አውሮፕላኗንም በጣሊያን በምትገኝበት ስፍራ ሄደው መጎብኘታቸውን ገልጸው አውሮፕላኗ የአገር ቅርስ ስለሆነች ማስመለስ እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም መጽሃፉ የአቬሽንን ታሪክ በሚገባ በመሰነድና የዘርፉን ታሪክ በማሳወቅ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
መጽሃፉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የሚባሉትን የጥናትና ምርምር የመረጃ አሰባሰብ የተከተለና ለአንባቢያን በሚስብ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።
የታሪክ ምሁሩ ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው መጽሃፉ በከፍተኛ ጥራት የተለያዩ ዋቢ መጽሃፍትና መረጃዎችን በማጣቀስ የተዘጋጀ መሆኑን ይናገራሉ።
መጽሃፉ ከ140 በላይ ታሪካዊ ምስሎችን ያካተተ መሆኑን ገልጸው ይህም የመጽሃፉን የታሪክ አስረጂነት ደረጃ ጠንካራ እንደሚያደርገው ነው ያብረሩት።
በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለተሰራችው ጸሃይ አውሮፕላን ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ ጠቁመው አውሮፕላኗን ለማስመለስ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮጀክት ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ታደለ ፋንታው መጽሃፉ ቅርስ ስለሆነችው አውሮፕላን ጠቃሚ መረጃ ይሰጣል ብለዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ ሰለተሰራችው 'ጸሃይ' አውሮፕላን ተጨማሪ መረጃዎችን የማሰባሰብና የማጥራት ሥራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ቅርሷን ለማስመለስ የሚደረጉ ይፋዊ እንቅስቃሴዎችን በቀጣይ የሚያሳውቅ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በሳይንሰ አካዳሚ ፕሬስ የታተመው ይኸው መጽሃፍ 336 ገጾች ያሉት ሲሆን 13 ምዕራፍ የተከፋፈለ ነው።