በደደርና አካባቢው አራት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ - ኢዜአ አማርኛ
በደደርና አካባቢው አራት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 15/2013(ኢዜአ) በምስራቅ ኢትዮጵያ ደደርና አካባቢው አራት ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ባለሙያ አስታወቁ።
በዩኒቨርሲቲው የጂኦፊዝክስ ህዋ ሣይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዳይሬክተርና የመሬት መንቀጥቀጥ ባለሙያ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክስተቱ በዋናነት በደደርና አካባቢው ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት 54 ደቂቃ አካባቢ ነው፡፡
ለአንድ ሰኮንድ የቆየው የመሬት መንቀጥቀጥ አራት ሬክተር ስኬል የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡
ክስተቱ በድሬዳዋ ፣ሀረማያና ሐረር መሰማቱን ተናግረው በተለይ በፎቅ ውስጥ ለነበሩት ሰዎች ክስተት ይበልጥ ሊሰማቸው ይችላል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ከተሞች አልፎ አልፎ የመሬት መንቀጥቀጥ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ጠቁመው በከተሞቹ ችግሩን ለመቋቋም ማዕከል ያደረገ ግንባታ መከናወን እንዳለትም አመልክተዋል፡፡
“ክስተቱን መተንበይ አይቻልም፤ ነገር ግን አልፎ አልፎ ይከሰታል በሚል መዘንጋት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል” ብለዋል፡፡
በመሬት መንቀጥቀጡ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል፡፡
የድሬዳዋ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ በተሰማቸው ወቅት ግራ እንዳጋባቸው ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የገንደ ቆሬ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሩቂያ አሊ በሰጡት አስተያየት ፤ጠረጴዛ ላይ የነበሩት ቁሶች ሲንቀሳቀሱ ተመለከትኩ፤ ንዝረትም ተሰማኝ፤ አላህ ምህረቱን ያውርድልን ብዬ ፀለይኩ ብለዋል፡፡
አራተኛ ፎቅ ላይ ስለነበርን መስተዋቶቹ ሲንቀጠቀጡ ግራ ገባኝ፤ እኔና ጓደኛዬ ተደናግጠን ወደ ታች ተፋጥነን ወርደን ያሉት ደግሞ ድሬዳዋ ለስራ የመጡት የፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን ሾፌር አቶ ፍቃዱ ሽፈራው ናቸው፡፡
“አሁን ተረጋግተህ ሣይሆን በወቅቱ ክስተቱ ያስፈራ ነበር” ብለዋል፡፡
ባለፈው ሣምንትም ሶስት ሬክታር የተመዘገበበት ተመሣሣይ የመሬት መንቀጥቀጥ በምስራቁ ክፍል መከሰቱ ተመልክቷል፡፡