በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚተከሉ 50 ሺህ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው -ፓርኩ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የሚተከሉ 50 ሺህ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው -ፓርኩ
ጎንደር ፣ ሚያዚያ 15/2013 (ኢዜአ) የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅ የሚያግዙ ከ50 ሺህ በላይ ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች ለተከላ እየተዘጋጁ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አበባው አዛናው ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጭው ክረምት ለተከላ የሚውሉት ሀገር በቀል የዛፍ ችግኞች በአምስት የችግኝ ጣቢያዎች የተፈሉ ናቸው፡፡
እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች ለፓርኩ አካባቢ ስነ-ምህዳር ተስማሚና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ግንቦትና ሰኔ ወራቶች የችግኝ መትከያ ጉድጓችዶች ቁፋሮ እንደሚካሄድና ከሀምሌ 5 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ ተከላ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።
በዘንድሮ ክረምት በፓርኩ የተፈጥሮ ሀብት መመናመን በሚስተዋልበት 25 ሄክታር በሚሸፍን ቦታ ላይ ተከላው እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት አመታት የፓርኩን ስነ-ምህዳር በጠበቀ መንገድ ከተተከሉ ከ80ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞች መካከል 60 በመቶ ያህሉ መጽደቃቸውን አመልክተዋል፡፡
የተተከሉት ችግኞች ከሁለት አመት በፊት በፓርኩ ክልል ደርሶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ የተጎዱ ሀገር በቀል ዛፎችን ለመተካት አስተዋጾ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በ1ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ሀብት ላይ ደርሶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ የተጎዱ የጓሳ ሳርና የቁጥቋጦ ዛፎች በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ማገገም እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ የፓርኩ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው ናቸው፡፡
የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አየነው በበኩላቸው የፓርኩ ስነ-ምህዳርና ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ በኩል 8ሺህ የማህበሩ አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በፓርኩ ውስጥ የተተከሉ ሀገር በቀል ችግኞችን በመጠበቅና በመንከባከብ አባላቱ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የዩንየኑ አባላት በመጭው ክረምት የችግኝ መትከያ ጉድጓችን በመቆፈርና በመትከል ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡
ፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ የብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፋት መገኛ ስፍራ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡