ኃያላን የሚጓተቱባት አገር

80

ኃያላን የሚጓተቱባት አገር

በሰለሞን ተሰራ

ሚያዚያ 15/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል የህወሃት ጁንታ በቀሰቀሰው ጸብ አጫሪነት የተፈጠረው ውጥንቅጥ ሰፋ ያለ ምልከታን የሚሻና የተለያዩ አካላትን ውስጣዊና ውጫዊ ፍላጎት ያገናዘበ ሊሆን ግድ ይላል፡፡

በክልሉ የሚካሄደው የሰላም ማስከበር ሂደት ሁለት ጽንፍ ያለውና የተራራቀ ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረግ ነው፡፡

ቀዳሚው መሬት ላይ ወርዶ የሚታየው የፊት ለፊት ውጊያው ሲሆን ሁለተኛው ድብቅ ሴራን ለማሳካት በማህበራዊ ትስሰር ገፆች የተከፈተና አደገኛ መልዕክቶችን በማሰራጨት አለም አቀፍ ተቀባይነት ለማግኘትና ተፅዕኖ ለማሳረፍ ያለመ መሆኑን ሩሲ (RUSI) በተባለ ድረገጽ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ የሚታየው አካባቢያዊና የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ ኃያላን አገራት በተለይ አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ በአደባባይ ሌሎች ደግሞ ከኋላ ተደብቀው የሚያራመዱት ነው፡፡ 

እነዚህ አለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገራት ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ለማባባስ የራሳቸውን ሚና  በመጫወት ላይ መሆናቸውን በካናዳ የአለም አቀፍ ደህንነት ፕሮፌሰርና የባልሲል አለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አና ፊዝ ጌራልድ እና በክዊን ዩኒቨርሲቲ የአለም አቀፍ ፐብሊክ ፖሊሲ አማካሪ እንዲሁም የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ዋና ኃላፊ በመሆን ያገለገሉት ሁግ ሴጋል ተናግረዋል፡፡

የፉክክር ታሪክ

የህወሃት ጁንታ አስቦና አቅዶ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መንግስት ወደ ህግ ማስከበር ለመግባት ተገዷል።

ነገር ግን "የማህበራዊ ሚዲያ አርበኞች ህወሃት የፈፀመው ተግባር ራስን ለመከላከል የተደረገ ነው" በማለት ቡድኑን የክህደት ጥግ ቅዱስ አድርገው በማሳየት አለምን ለማሳሳት እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ በክልሉ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና በኤርትራ ጦር የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተፈጽሟል በማለት በገንዘብ በገዟቸው የመገናኛ ብዙሃን ቡድኖች አማካኝነት የውሸት ትርክታቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ።

መገናኛ ብዙሃኑንና አጋሮቻቸው ከትግራይ ክልል ነዋሪ መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሰብዓዊ አቅርቦት እያገኘ አይደለም በማለት የሚጽፉ ሲሆን የቡድኑ ቃል አቀባይ ነኝ የሚል ግለሰብም ከተደበቀበት ዋሻ ሆኖ ህዝቡ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር መዘጋጀት አለበት የሚል መልዕክት በማስተላለፍ በቀቢፀ ተስፋ እየቀሰቀሰ ይገኛል፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሆነ ህዝብ እርዳታ ማድረሱን አስታውቋል፡፡

በክልሉ በአክሱም ከተማ ተፈጸመ የተባለው ጭፍጨፋ መሰረተ ቢስና የውሸት ቅንብር ማረጋገጫ ያልተገኘለት ሲሆን አንዳንድ ምዕራባዊያን የመገናኛ ብዙሃን ይህንኑ ያልተረጋገጠ መረጃ በማስተጋባት ተጠምደዋል፡፡

የህወሃት በቡድን በክልሉ የኤርትራ ወታደሮችን መለያ ልብስ በማዘጋጀት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ጥቃቱ በኤርትራ ወታደሮች እንደተፈጸመ አድርጎ የሚያቀርበውን የቁራ ጩኽት እነዚሁ መገናኛ ብዙሃን መልሰው ያስተጋቡለታል፡፡

በክልሉ ለሚታየው ውጥንቅጥ ዋነኛው ምክንያት በክልሉ ከሚገኙ በተለይም ከመቀሌ እስር ቤት የተለቀቁት ወንጀለኞች መሆናቸው የአደባባይ ሐቅ ቢሆንም ወንበዴዎቹ እውነታውን በመካድ እጃቸውን ወደ ሌላ አካል ላይ ቀስረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት፤ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመካድ ያልተጨበጠ ክስ እያቀረቡ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የዚህ ምክንያት ደግሞ ህወሃት ቀደም ብሎ የዘረጋው የአንድ ለአምስት የስለላ ጥርነፋ እንደሆነም ይናገራል፡፡

የህወሃት ጁንታ ቀደም ሲል በክልሉ ከ 250 ሺህ ያላነሱ ገበሬዎችን ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ሚሊሻ በሚል ስም በህገ ወጥ መልኩ የጦር መሳሪያ ማስታጠቁም ይታወቃል፡፡

መንግስት በዚህ ፅንፈኛ ቡድን ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ ከወሰደ በኋላ የተበታተነው የጁንታው ታጣቂ ሃይል ወደ ሽምቅ ውጊያ ለመግባት እየተጣጣረ ይገኛል።

ይህንን ሃይል ነው እንግዲህ አንዳንድ ምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን የጁንታው ሃጥያት ፅድቅ አስመስለው በመንግስት ላይ ወቀሳ የሚያቀርቡት፡፡

ለትግራይ ክልል ውስብስብ ችግሮች እውነታ መታወቅ እንዳለበት የሚወተውቱ ፀሃፊያን ግን በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት ይላሉ፡፡

የብዙዎች ፍላጎት የሚንፀባረቅበት የጥቅም ትንቅንቅ

ችግሩ መከሰቱን ተከትሎ አንዳንድ የአፍሪካ አገራትና የረጅም ጊዜ ወዳጅ የነበሩ ምዕራባውያን አገራት ጭምር ራሳቸውን በማግለል አንዳንዴም ያልተገባ አስተያየት ሲሰጡ መመልከት አስገራሚ አይሆንም፡፡

ለዚህ ምላሽ ከመስጠት በፊት በቀጠናው ያለውን በውኃና በተፈጥሮ ሐብት ላይ የተመሰረተ የጂኦፖለቲካ ፉክክርን መመርመር ግድ ይላል፡፡

ግብፅ እና ሱዳን ከህዳሴው ግድብ ግንባታን የውኃ አሞላል ጋር በተያያዘ ተቃውሟቸውን በአደባባይ በማሰማት ላይ ሲሆኑ ሱዳንም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቃ በመግባትና ገበሬዎችን በማፈናቀል በወረራ መሬት ይዛለች፡፡

ግብፅም ኢትዮጵያን በተመለከተ የምታቀርበው ጸረ ሰላም ታሪክና ድርሻዬ በማለት የምታላዝንበት የውሃ ክፍፍል ከተነካ "ወዬውላችሁ" በማለት መፎከሯን ቀጥላለች፡፡

ሁለቱ አገራት ጫናቸውን ለማጠናከር የትግራይ ቀውስ ከተጀመረ ከጥቂት ቀናት በኋላ የጋራ የጦር ልምምድ እስከ ማድረግ ደርሰዋል፡፡

ሁለተኛው የጦር ልምምድ ደግሞ የግድቡ ቀጣይ ውይይት ከሚደረግበት ቀናት ቀደም ብሎ ከ15 ቀናት በፊት መጋቢት 28 ቀን ተደርጓል፡፡

አለም አቀፍና አህጉራዊ ተዋናዮች በግድቡ ዙሪያ መግባባት ላይ እንዲደረስ እየሰሩ ቢሆንም ነገሩ መቋጫ አላገኘም፡፡

ግድቡን በተመለከተ የተለያዩ አካላት የራሳቸውን ፍላጎት ለመጫን እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን እስራኤልም የሯሷን ፍላጎት በማስቀደም ግብፅ የናይልን ወንዝ ወደ ሲናይ በረሃ እንድታሸጋግርላትና በደቡብ እስራኤል የሚገኘውን የኔጌቨን በረሃ ማልማት ትፈልጋለች፡፡

የአፍሪካ ህብረት አሁንም ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡


የኃያላን አገራት ጣልቃ ገብነት

በርካታ አገራት ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ የያዘችውን አቋም ለማስቀየር አብረው እየሰሩ ሲሆን አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደርም ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው የተባሉትን ሴናተር ክሪስ ኮን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር እንዲነጋገሩ አድርጓል፡፡

ከአጀንዳዎቹ መካከል የህዳሴው ግደብ አንዱ እንደሚሆንም ፀሐፊዎቹ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አሜሪካ በቀጠናው የተፈጥሮ ሐብት ላይ ያላትን ፍላጎት ለመረዳት ጉብኝቱ ብቻውን በቂ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡

በአሜሪካና በቻይና መካከል ያለው ፋክክር እየተካረረ መምጣቱም ይታወቃል፡፡

በተለይ ቻይን በምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ የመረጃ ዘመን ቴክኖለጂ መርህ፣ የሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሸቲቭ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የኢንቨሰትመንት ተሳትፎ በመታገዝ በአፍሪካ የበላይነት ይዛለች፡፡

አሜሪካም በአፍሪካ ያጣችውን የበላይነት ለማስመለስ አበክራ ለመስራት ቆርጣ መነሳቷ ሁኔታውን አስጊ አድርጎታል፡፡

ይህንኑ ከግንዛቤ ከከተትነው በትግራይ የሚታየው ግጭት የውጭ አካላት የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነት ያለበት መሆኑን ከመረዳት ባለፈ በኢትዮጵያ የሚገኙ ፖሊሲ አውጪዎች ላይ ተፅእኖ በማሳደር እጃቸውን ለመጠምዘዝም ያለመ መሆኑን ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ መንግስት ጋር ያወረደው ሰላም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላት ሲሆን አሁን ላይ የውስጥ ሰላሙን ለማደፍረስ በህወሃት ጁንታ የተከፈተበትን ጠብ አጫሪነት በማክሸፍ እውነታውን ለማሳየት ጠንክሮ መስራት አለበት፡፡

መንግስት በትግራይ የመሸጉትን አምባገነን ወንበዴዎች ከመዋጋት ጎን ለጎን መጪውን ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ አለበት፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን አለማዋን እንድታሳካ ወይም አላማዋን ለማስቀልበስ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጣት ድጋፍ ምን እንደሆነ ስለማይታወቅ በቅድሚያ ለሚመጣው ነገር መዘጋጀት ይጠበቅባታል፡፡

ሁሉም የራሱን ፍላጎት ለመጫን ስለሚወራጭ ኢትዮጵያ የራሷን ፍላጎትና ግብ እውን ለማድረግ ቁርጠኛ ከመሆን ባለፈ በምንምና በማንም ኃይል ወደ ኋላ ማፈግፈግ የለባትም፡፡

ምዕራባውያን አገራት በአፍሪካ ቀንድ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያለፈ እውነተኛ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ፍላጎት ካላቸው በትግራይ ያለውን ችግር በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት መቻኮል የለባቸውም፡፡

በአንፃሩ አገሪቱ የጀመረችውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የፖለቲካ ለውጥ እንዲሁም በግድቡ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር እንዲሳካ ማገዝ አለባቸው፡፡

ይህንን ማድረግ ከቻሉ ለቀንዱ አገራት ብልፅግና ታላቅ መሰረትን ይጥላሉ፡ ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ አካባቢውን ለሰርጎገቦች አሳልፎ በመስጠት አህጉሪቱን ለበለጠ ብጥብጥ ይዳርጓታል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ እውነተኛ ደሞክራሲ ለመሸጋገር በለውጥ ሂደት ውስጥ ሆና ህዝቦቿን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማሸጋገር በጀመረችው ልማት አሁንም "ኃያላን የሚጓተቱባት አገር" መሆኗ ለበርካቶቻችን እንቆቅልሽ ሆኗል።

በህዋሃት ጁንታ ተላላኪዎች የሚራገበው የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻም የህዳሴ ግድቡን እውነታ በማዛባት ኃያላን አገራት የአፍሪካን አንጡራ ሐብት እንደልባቸው እንዲዘርፉ የሚያስችል የክህደት ጥግ መሆኑን ልብ ይሏል።

ኃያላን አገራት አፍሪካን ተጠቃሚ በማድረግ ከእድገቷ እነሱም ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ የጋራ እሳቤን በማራመድና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን መደላድል በመፍጠር ስጋቱን ተስፋ ማድረግ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም