አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበት አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄና ጉባኤ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበት አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄና ጉባኤ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13/2013 (ኢዜአ) አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበት አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄና የምክር ቤቱ ዓመታዊ ጉባኤ የፊታችን አርብና ቅዳሜ የሚካሄድ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ ዘርፉ የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት አውታሮችን፣ ፋብሪካዎችንና የመኖሪያ ቤቶችን ለማስፋፋትና ለማልማት ያስችላል።
በተጨማሪም የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚያዊ እድገቱ ላይ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
ዘርፉ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ልክ ሚናውን ለመወጣት የ10 እና የ5 ዓመት እንዲሁም የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታዎች መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።
ይህንንም መሰረት በማድረግ የዘርፉ ተዋንያን የሚያሳትፈውና አገር አቀፍ ንቅናቄና ጉባኤ ዘርፉን ለማነቃቃት ይረዳል ብለዋል ኢንጂነር አይሻ።
በጉባዔው ላይ የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታን ጨምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበትና ፕሮጀክቶች በጥራት፣ በጊዜና በተመጣጣኝ ወጪ የሚፈጸምባቸው አማራጮች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው እየተስተዋሉ ያሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይም የሚያተኩሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተመልክቷል።
ባለድርሻ አካላት በኮንስትራክሽን ፖሊሲና በማስፈጸሚያ ስልቶች ላይ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙና በቅንጅት የሚመሩበት ምቹ መደላድል እንደሚመሰረትም ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች፣ መሐንዲሶች፣ ግብዓት አምራቾችና አቅራቢዎች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።