የሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠራ ሥራዎች ጥቅም ላይ እንዲውል የሁሉንም ተቋማት ጥረት ይጠይቃል …የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል

1561

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 11/2013 (ኢዜአ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠራ ሥራዎች ለአገር ጥቅም እንዲውሉ ሁሉንም ተቋማት የበኩላቸውን ድርሻ  እንዲወጡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ጠየቀ።

ለተከታታይ አራት ቀናት ሲካሄድ የቆየውና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የሰው ሰራሽ አስተውሎት አውደ ጥናትና ዓውደ ርዕይ ተጠናቋል።

በአውደ ጥናትና ዓውደ ርዕዩም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከልና ሌሎች ተቋማት ያቀረቧቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውጤቶች ተጎብኝተዋል።

በዓውደ ርዕዩ ላይ ወጣቶች ያቀረቧቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመፍትሄ ሃሳቦች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚደረግም ተገልጿል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰው ልጆች በተፈጥሮና በህይወት ኡደት የሚያገኟቸውን የማመዛዘን፣ ምክንያታዊ የመሆን፣ የማሰብ፣ የመማር፣ የመገንዘብና በቋንቋ የመግባባት ክህሎቶችን በረቀቀ ቀመር ማሽኖችን በማስተማር የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ በግብርና፣ በአይ.ሲ.ቲ፣ በሚትዮሮሎጂ፣ በትምህርት፣ በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት፣ በኤሮስፔስ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የፈጠራ ውጤቶች ለአገር ጥቅም እንዲውሉ ሁሉም ተቋማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የማዕከሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታየ ግርማ በበኩላቸው በዓውደ ጥናትና ዓውደ ርዕዩ ላይ በተቋማት የነበሩ ተግዳሮቶች በጥልቀት መዳሰሳቸውን ገልጸዋል።

ለተለዩት ተግዳሮቶችም ማዕከሉ ከዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችና ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር በመሆን የመፍትሄ አቅጣጫ መቀመጡን አመላክተዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው “መሰል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎችና ሃሳቦች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን መፍታት እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በግብርና፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰሩ ፈጠራዎችን ወደ ምርት የሚቀይሩ አካላትን ለመደገፍ የፖሊሲ፣ የህግና የገንዘብ እገዛ እንዲያገኙ ከድርጅቶችና ተቋማት ጋር  እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ማዕከሉ ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ጋር በትብብር በመስራቱ የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

መርሃግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል በ2012 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 463/2012 ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ መቋቋሙ ይታወሳል።