ለአገራችን ሰላም የጋራ ስራ ይጠበቅብናል- የጎህ 2013 የሰላምና አንድነት ተሸላሚዎች

101

ሚያዚያ 11/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ሁላችንም የጋራ ስራ ይጠበቅብናል ሲሉ የጎህ 2013 የሰላምና አንድነት ተሸላሚዎች ተናገሩ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው ጎህ የ2013 የሰላምና አንድነት ሽልማት በኢትዮጵያ ለሰላምና አንድነት ጉልህ አስተዋፅኦ የነበራቸው 12 ግለሰቦች ተሸልመዋል።

በመርሃ ግብሩ ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በሰላምና በአንድነት ስራዎች ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸው ግለሰቦች ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ተሸላሚዎቹ በሰላም ግንባታ ሂደት የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉና ስለሰላም ብለው ብዙ የሰሩ፣ ያስተማሩና አርአያ የሆኑ ሰዎች ናቸው ተብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሰላምን ለማምጣት የግለሰቦች ጥረት ብቻ የትም አያደርስም።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እንደህዝብ ስለ ሰላም ማሰብ ስለ ሰላም መስራት የሁሉም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የሽልማቱ አዘጋጅ የኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይንመንት ኦርጋናይዘር ስራ አስኪያጅ አቶ ሞቲ ሞረዳ በበኩላቸው ሰላም እንደ ውሃና አየር ለሁሉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

"የሰላም ዋጋ የማይተመን እና ብዙዎቻቸን ካላጣነው የማናስተውለው ውድ ሃብት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሁላችንም የሰላም ጠበቃ ሆነን መቆም ይኖርብናል ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከትግራይ፣ ከአፋር ክልል አቶ መሀመድ ያዬ፣ አቶ ፈንታ ጫኔ ከአማራ፣ ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከኦሮሚያ፣ አቶ መሀመድ ጋራድ ከሱማሌ፣ አቶ ያደሳ ዳቢ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ቄስ ተክሉ ደንኮሌ ከሲዳማ ጎህ የ2013 የሰላምና አንድነት ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።

የጋሞ አባቶች ከደቡብ ክልል፣ አቶ አየለ ተስፋዬ ከሀረሪ፣ አቶ ቶማስ ቱት ከጋምቤላ እንዲሁ ተሸላሚ ሆነዋል።

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር እንድሪስ አና ሃጅ ከድር አባስ ከድሬዳዋ ከተማ ተሸላሚዎች ናቸው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሸላሚዎችም ለአገራችን ሰላም ሁላችንም በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም