ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በመስራት ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባ ተጠቆመ

1175

ሚያዚያ 11/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በመስራት ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚገባ ተገለጸ። ለስፖርት ጋዜጠኞች በስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች የታገዘ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዲስ አበባ መሰጠት ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ከሚሽነር ባላይ ደጀን በስልጠናው ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው በማስቻል የስፖርት ጋዜጠኞች ጉልህ ደርሻ አላቸው።

ኮሚሽነሩ አክለውም  ጋዜጠኞች ተተኪና ሀገርን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራትና ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ትልቅ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሁሉም አካባቢዎች የማህበረሰብ የጤናና የአካል ብቃት ስፖርት እንዲስፋፋ የስፖርት ጋዜጠኞች ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲጠናቀቁና አዳዲስ የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲገነቡ የስፖርት ጋዜጠኞች አሻራቸውን እያሳረፉ መሆኑንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረውና ሀገርን የሚወክሉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ንዋይ ይመር፤ የአሁኑ ስልጠና ጋዜጠኞች በሚሰሩት ስራ ላይ ተጨማሪ እውቀት እንዲኖራቸው አጋዥ መሆኑን ገልጿል።

ለሀገሪቱ ስፖርት እድገት ድርሻው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገረው።

የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በጋራ ያዘጋጁት ስልጠና በስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎችና በጋዜጠኞች የታገዘ የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው።

ለ20 ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ እየተሰጠ ያለው ስልጠና ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል።