በድሬዳዋ ለመገንባት የተዘጋጁት ፋብሪካዎች ወደ ብልጽግና ጎዳና የመሸጋገሪያ ማሳያ ናቸው - አደም ፋራህ

79

ድሬዳዋ ፤ሚያዚያ 11/2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ለመገንባት የተዘጋጁት የሲሚንቶና ብረት ማቅለጫ ዘመናዊ ፋብሪካዎች ለሀገር መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡና ወደ ብልጽግና ጎዳና የመሸጋገሪያ ማሳያ መሆናቸውን የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ።

በድሬዳዋ 350 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ለሚገነቡት ለእነዚሁ የብረት ማቅለጫና የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ትናንት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።


አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ እንዳሉት፤ ፋብሪካዎቹ የውጭ ምንዛሬ የሚያድኑና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ትስስር የሚያጠናክሩ ናቸው።


ለሀገርና ትውልት መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡና ወደ ብልጽግና ጎዳና የመሸጋገሪያ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

የሀገሪቱ የግንባታው ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣትን ተከትሎ የተከሰተውን የግንባታ ዕቃዎች እጥረት ለመፍታት ዘመናዊ ፋብሪካዎች የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፤ ድሬዳዋ ከጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ፤ መሠረተ-ልማቶች ተሟልተው የሚገኙበት፣ በታታሪነትና አንድነት ተባብሮ የሚኖር ህዝብ ማዕከል በመሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭነቷን ያጎላዋል ብለዋል፡፡

የፋብሪካዎቹ መገንባት ሥራ አጥነትና የግንባታ ግብአት ችግር እንደሚያቃለል ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ፤ በኢትዮጵያዊው ባለሃብት የሚመራው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ኩባንያና በቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ኩባንያ ጥምረት የሚገነቡት ግዙፍ ፋብሪካዎች ለሀገሪቱም ሆነ ድሬዳዋ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ብለዋል፡፡

ባለሃብቱ አቶ ብዙአየሁ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካዎቹ በቀን 5 ሺህ ቶን ሲሚንቶ እና በዓመት 300 ሺህ ቶን ብረት የማምረት አቅም አላቸው፤ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡

በአጭር ጊዜ ግንባታቸውን የሚጀምሩት ፋብሪካዎቹ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ሥራው እንዲከናወን የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የፌደራል መንግስት ፣ ሱማሌ ክልልና ድሬዳዋ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አመልክተዋል፡፡

ለፋብሪካዎቹ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጡ ሥነ-ሥርዓት የፌደራልና የክልል ክፍተኛ አመራሮች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና ኃይማኖት አባቶች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም