የኢጋድ የካንሰር ህክምና የልህቀት ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በአዲስ አበባ ተቀመጠ

1023

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11/2013 (ኢዜአ)  ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት /ኢጋድ/ የካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።

በ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው ይህ ማዕከል ከቀጣናው አገራት ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ካንሰርን ለመዋጋት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመሰረት ድንጋዩን በጋራ አኑረዋል።

ማዕከሉ በቀጣናው እያደጉ የመጡ ከካንሰር ጋር የተያያዙ የጤና አጠባበቅ ችግሮችን ለመቋቋም፣ ካንሰርን ለመከላከልና ለማከም ብቁ ባለሙያዎች ለማሰልጠን እንደሚቋቋም ተገልጿል።

ዶክተር ወርቅነህ  ገበየሁ ማዕከሉ በቀጣናው የካንሰር በሽታን አስቀድሞ በመከላከልና ኅብረተሰቡን ከካንሰር ለመጠበቅ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በአባል አገራቱ በጤና ዘርፍ የተያዙ አጀንዳዎችን እውን ማድረግ ያስችላልም ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በበኩላቸው ማዕከሉ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአባል አገራቱ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የካንሰር ሕክምና መስጫ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የስልጠናና የምርምር ማዕከል በመሆንም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የማዕከሉን ግንባታ ሃሳብ ያመነጩ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች አመስግነዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅ በተለይም ካንሰርን ለመከላከልና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም  አስተዋጽኦው የላቀ ይሆናል ብለዋል።

አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የካንሰር ምርመራ፣ ሕክምና፣ ጥናትና ምርምርን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥራት ያለው የካንሰር እንክብካቤ አገልግሎቶችን ይሰጣል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማዕከሉ የሚገነባበትን 200 ሺህ ሜትር ስኩዬር መሬት በነጻ መስጠቱም ተገልጿል።