ህንድ በኢትዮጵያ ሀድያ ዞን የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ትደግፋለች… አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ

114

ሆሳዕና፤ሚያዝያ 11/2013 (ኢዜአ) ህንድ በኢትዮጵያ ሀድያ ዞን የሚከናወኑ የልማት ስራዎች እንደምታግዝና ባለሀብቶቿ በዞኑ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ አስታወቁ።

አምባሳደሩ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጋር በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ወቅት አምባሳደሩ እንዳሉት ሀገራቸው በዞኑ በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን ትደግፋለች።

በትምህርት መስክ ህንድ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ሮበርት፤ከዚህ በተጨማሪ በመምህራን ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

በዞኑ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጥናት የህንድ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም ተናግረው፤በማህበራዊ ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ሀገራቸው ለማገዝ ፍላጎት እንዳላት አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው መንግስት በኢትዮጵያና ህንድ መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በትምህርት መስክ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከህንድ መንግስት ጋር ባለው ትብብር የትምህርት እድል አግኝተው መማር እንደቻሉና ትብብሩ ዛሬም ተጠናክሮ እንደቀጠለም ገልጸዋል።

የትምህርቱን ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል በመምህራን ልማትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል ።

የህንድ ባለሀብቶች በዞኑ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ሚኒስትሯ አመላክተዋል።

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው “ዩኒቨርሲቲው በ2020 በሀገሪቱ ከሚገኙ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ከህንድ መንግስት ጋር የተደረሰው ስምምነት ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

የሀድያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዶክተር አበበ ሎላሞ በበኩላቸው የዞኑ አስተዳደር በተለያዩ የልማት መስኮች መሰማራት ለሚፈልጉ የህንድ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንግ የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲንና የንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል።