የዩኒቨርሲቲዎችን የምርምር ስራዎች ለመደገፍ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል-- የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች

59

ሚያዚያ 10/2021 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዩኒቨርሲቲዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በሌሎችም ስራዎች ላይ የሚያከናውኗቸውን ምርምሮች እንደሚያግዝ የከፍትኛ ትምህረት ተቋማት ፕሬዘዳንቶች ገለጹ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አዲስ ያስገነባው የዋና መሥሪያ ሕንፃ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ትናንት በይፋ ተመርቋል።

በዛሬው እለትም የተለያዩ የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች የተቋሙን አዲስ ህንጻ እና በውስጡ የሚከናወኑ ተግባራትን ጎብኝተዋል።

የኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ቢሮዎች፣ የምርምር ማእከሎችን፣ ላብራቶሪዎችን እንዲሁም ከ7 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊዎች የምርምር ሥራ የሚያከናውኑበት የሳይበር ልማት ማእከልን በውስጡ ይዟል።

ይህም በተለይ የአገሪቱን እድገት ከማጠናከሩም በተጨማሪ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር ስራዎቻቸውን ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንቶች ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎችንም የምርምር ስራዎች ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወስጥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በመሳሰሉት መስኮች የተሻለ እውቀት እና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ለማበረታታት እና የተሻለ እድል እንዲፈጠርላቸው ያግዛልም ነው ያሉት።      

በዘርፉ ተገቢውን ውጤት ለማምጣትና በርካታ ባለሙዎችንም ለማብቃት በሚደረገው ጥረት  የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት እና የምርምር ኢኒስቲትዩቶች ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር ተቀናጅተው መስራት አለባቸው ብለዋል።

ይህም ፍላጎት እና አቅም ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት አቅማቸውን እንዲፈትሹ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።  

አዲሱ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ግንባታ በ2002 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በ23 ሺህ 371 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እና ከ14 እስከ 17 ወለል ያላቸው 5 ብሎኮችን የያዘ ነው።

ሕንፃዎቹ በውስጣቸው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ የሰላም ሚኒስቴር፣ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከልን እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማእከልን ያካታቱ እንደሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም