በግብርና ዘርፍ የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ምርታማነትና ጥራት እንዲሻሻል ያደርጋል-- ምሁራን

95

ሀረር ሚያዝያ 10 /2013 (ኢዜአ) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በግብርና ዘርፍ የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ ምርታማነትና ጥራትን ለማሻሻል አስተዋጻ የሚያደርግ መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።

ምሁራን፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ልዑክ በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ፕሮግራሞች ስርዓተ ትምህርት ክለሳ  አውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ባለሙያ አቶ በሱፍቃድ ሀይለማርያም ምሁራንን፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በሀገሪቱ በሰባት ማእከላት የመጨረሻ ምእራፍ የስርአተ ትምህርት ቀረፃና ማረጋገጥ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ፕሮግራሞች የስርአተ ትምህርት ክለሳ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጤና ፣ በደብረማርቆስና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች የኢንጅነሪንግ፣ እንዲሁም በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ፕሮግራሞች ስርአተ ትምህርት ክለሳ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

"ከስርአተ ትምህርት ቀረፃና ማረጋገጥ ሂደት ጋር ተያይዞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች መካተታቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በዓለምና በሀገር አቀፍ የሰው ሃብት ገበያ ውስጥ ተፈላነታቸው እንዲጎለብት የማድረግ ሚና ይኖረዋል" ብለዋል፡፡

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንግስቱ ኡርጌ ከግብርናው ጋር ቅርበት ባላቸው የትምህርት መስኮች የመጨረሻ ምእራፍ የስርአተ ትምህርት ቀረፃና ማረጋገጥ ተግባር መካሄዱን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲው በ3ኛና በ4ኛ አመት የሚሰጡ 13 የትምህርት ፕሮግራሞች ስርአተ ትምህርት ስለመገምገማቸውን ጠቁመው ስርአተ ትምህርቶቹ ከ45 ቀን በኋላ ወደ ተግባር እንደሚገቡ አመላክተዋል፡፡

"ስርአተ ትምህርቶቹ  የሀገሪቱን ትምህርት ጥራት ከማጎልበት አንፃር ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል" ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሰለሞን አባተ በበኩላቸው የተደረገው የስርዓተ ትምህርት ክለሳ በግብርናው ዘርፍ ከቀለም ትምህርት ባለፈ በተግባር የተደረፈ በመሆኑ ተማሪዎች ግብርናው የሚጠይቀውን እውቀትና ክህሎት እንዲይዙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስርአተ ትምህርቱ በግብርናው ዘርፍ በእፅዋት ሳይንስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ጥራትን ለማጎልበት እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል ።

በተለይም በዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ከማሰደግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ስርአተ ትምህርቱ ተመራቂዎች በምርምርና በሌሎች ህብረተሰቡን በሚጠቅሙ የልማት ስራዎች ውጤታማ ተግባር መፈፀም በሚያስችል አግባብ የተቃኘ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ለስርአተ ትምህርቱ ተግባራዊነትና ውጤታማነት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት በትብብርና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

"ስርአተ ትምህርቱ  ሀገሪቷ ለምትፈልገው የሰው ሃይል ጥያቄ እንዲመልስ የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ሙሃመድ ወርቁ ናቸው ፡፡

ለውጤታማነቱ ከተዘጋጀው ዶክመንት በተጨማሪ በተለይም የተማሪዎች ተነሳሽነትና የተቋማዊ አደረጃጀት ወሳኝ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም