የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና መደገፍ ይገባል-- ባለድርሻዎች

200

አሶሳ፣ ሚያዚያ 10 / 2013 (ኢዜአ) በራስ ጥረት የሚከናወኑ የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና መደገፍ ይገባል ሲሉ የዘርፉ ባለድርሻዎች ገለጹ ።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ “በፈጠራ ላይ የተመረኮዘ ትውልድ መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ የፈጠራ ስራ ላካሄዱ እውቅና የሚሰጥ አውደ ጥናት ትላንት አካሂዷል፡፡

በአውደ ጥናቱ የፈጠራ ስራቸውን ካቀረቡት መካከል ወጣት እዩብ ያህያ ከልጅነቱ ጀምሮ የፈጠራ ፍላጎት እንደነበረው ለኢዜአ ተናግሯል፡፡

በአውቶሜሽን ኢንዳስትሪያል ዘርፍ የኮሌጅ ትምህርት መከታተሉን የሚገልጸው ወጣቱ ከወዳደቁ የተሸከርካሪ አካላት ባለአራት እግር ተሸከርካሪ መስራቱን አመልክቷል፡፡

በግል ስራውን በሚያንቀሳቀስበት ወቅት ለትራንስፖርት በየዕለቱ የሚያወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቆጠብ ማሰቡ ለፈጠራ ስራው ምክንያት እንደሆነው አመልክቷል።

"አፍሪካዊያን መፍጠር እንደሚችሉ ለማሳየት ራዕይ አለኝ" ብሏል ወጣቱ፡፡

በሠራት ተሽከርካሪ የተሳካ ሙከራ ማድረጉን የሚናገረው ወጣት እዩብ የፈጠራትን ተሸከርካሪ በከተማው የሚጠቀም ቢሆንም ለድጋፍም ሆነ ሌላ ጉዳይ የጠየቀው አካል እንደሌለ ገልጻል፡፡

አውደ ጥናቱ ስራውን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነለት አመልክቷል፡፡

አርሶ አደር መሃመድ ሰይድ በበኩላቸው በስራቸው ወቅት የገጠማቸው የምርት ማጓጓዣ እጥረት የተለያየ መጠን ያላቸው ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች እንዲሠሩ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል፡፡

 በቤተሰብ ህመም ምክንያት ትምህርታቸውን ከሰባተኛ ክፍል እንዳቋረጡ አስታውሰዋል፡፡

ለፈጠራ ስራ መሠረቱ ተነሳሽነት እንደሆነ የተናገሩት አርሶ አደሩ የአቅም ውስንነት እንጂ ሌሎች የፈጠራ ስራዎችን በንድፈ ሃሳብ አዘጋጅተው ማስቀመጣቸውን ለኢዜአ አስረድተዋል፡፡

ድጋፍ የሚያደርግ አካል ባለመኖሩ ተጨማሪ የፈጠራ ስራዎችን ለጊዜው ማቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

በራሳቸው ተነሳሽነት በመሰል የፈጠራ ስራ የሚሳተፉትን መደገፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አርሶ አደር መሃመድ ተናግረዋል፡፡

በሰዓት እስከ አራት ሄክታር መሬት ውሃ ወይም ኬሚካል መርጨት የሚያስችል በጸሐይ ሃይል የሚሠራ መሳሪያ መፍጠሩን የገለጸው ደግሞ ወጣት ማቲዮስ አበበ ነው፡፡

"ሁሉም ሰው ሲፈጠር በውስጡ የፈጠራ ሃሳብ አለው" ያለው ወጣቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፈጠራ ስራዎች የሚደረጉ ድጋፎች መኖራቸውን አመልክቷል፡፡

በተለይ ወጣቶች የመንግስት ስራን ከመጠበቅ ይልቅ ለሃገር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ መሠል ስራዎችን ማከናወን አለባቸው የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ አውደ ጥናቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የፈጠራ አቅም ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በመድረኩ የቀረቡ ፈጠራዎችን በሚመለከተው አካል እውቅና እንዲያኙ ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የፈጠራ ስራዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ማላመጃ ማዕከል እንዲገነቡ እንደሚደረግ ጠቅሰው ማበረታቻው የፈጠራውን ባለቤቶችና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡

የእውቅና አውደ ጥናቱ ግብ የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና እውቅና እንዲያገኙ  ማስቻል መሆኑን ዶክተር ሃይማኖት አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም