በኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁሞ ምርጫውን ማካሄድ የተሻለ አማራጭ ነው - ምሁራንና ፖለቲከኞች

60

ሚያዚያ 9 / 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለምርጫው እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች ቢያጋጥሙም ችግሩን ለማለፍ ምርጫውን ከማካሄድ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ምሁራንና ፖለቲከኞች ገለጹ።

ምሁራን ከጎጥና ከመንደር አደረጃጀት ወጥተው አገራዊ ይዘት ባላቸው ጉዳዮች ጥናትና ምርምር በማድረግ የመፍትሄ አማራጮች ማቅረብ አለባቸውም ተብሏል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት "6ኛው አገራዊ ምርጫና የምሁራን ሚና" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከምሁራን ጋር መክሯል።

የኢትዮጵያ ነባራዊ የሠላምና የጸጥታ ሁኔታ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ እንዳይሆን ከማድረግ ባለፈ በሠላም እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሊፈጥር እንደሚችል ተነስቷል።

በደቡብ አፍሪካ ስታላንቦሽ ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ደስታ መብራቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሠላምና የጸጥታ ስጋት አንዣቧል።

እየተከሰተ ስላለው የዜጎች ሞት፣ መፈናቀል፣ ለዓመታት ያፈሩት ሀብትና ንብረት መዘረፍና መቃጠል ችግሮች 'ከበቂ በላይ አውርተንለታል' ያሉት ፕሮፌሰር ደስታ፤ "አሁን መሆን ያለበት የችግሩን መፍትሄ ማፈላለግና እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ነው" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በችግር ውስጥም ሆኖ የሕዝብን ድምጽ በማካተት በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

"ምሁራን አገራዊ ጉዳዮችን ከኅብረተሰቡ በተለየ ሁኔታ የማየት አቅም ስላላቸው ቀድመው የችግሩን መንስኤና የመፍትሄ አቅጣጫ ማመላከት አለባቸው" ብለዋል ፕሮፌሰር ደስታ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ ኅብረተሰቡ በአንድ በኩል በመረጥነው አካል እንተዳደራለን የሚል ተስፋ፤ በሌላ በኩል አገሪቷ ወደ ትርምስ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት መያዙን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ምርጫ ሲደላ ብቻ የሚካሄድ ሳይሆን በጦርነት ውስጥም ሆኖ ሊደረግ የሚችል በመሆኑ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የግድ መካሄድ አለበት ነው ያሉት።

ሕዝቡ ድምጹን ተጠቅሞ ይመራኛል ያለውን አካል መምረጥ ካልቻለ ተጨማሪ ችግር እንደሆነም ነው ሰብሳቢዋ ያብራሩት።

በመሆኑም መንግስት፣ ኅብረተሰቡና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሠላምና ጸጥታ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

አገር በቀል እይታ የተባለ ድርጅት መስራችና መሪ አቶ ጸደቀ አባተ ምሁራን አገር ችግር በገጠማት ጊዜ የችግሩን መንስኤ ከመለየት ባለፈ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርቡ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"ማንነትን መሰረት ያደረገ የእገሌ ብሔር ማኅበር፣ የእገሌ ብሔር ምሁራን የሚለው አደረጃጀት የምሁርነት መገለጫ አይደለም፤ ሊወገድ ይገባል" ነው ያሉት።

የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሳ አደም "ምሁራን በተለያዩ የምርምር ሥራዎች የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ፓርቲዎች ወደተሻለ መፍትሄ እንዲመጡ ጫና መፍጠር አለባቸው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም