"የአእምሮ ፈውስ" የተሰኘ መጽሐፍ ለምረቃ በቃ

75

አዲስ አበባ ሚያዚያ 09/2013 (ኢዜአ) ግለታሪክ ላይ ያተኮረና "የአእምሮ ፈውስ" የተሰኘ የፍቅርተ ደምሴ መጽሐፍ ዛሬ ምረቃ በቅቷል።

ግለታሪኳን በመጽሐፍ ጽፋ ያስመረቀችው ፍቅርተ ደምሴ መጽሐፉ ከልጅነት ሕይወቷ እስከ አሁን ያለውን ታሪኳን እንደሚያካትት ገልፃለች።

መጽሐፉን የማሳተሟ ዓላማ በጎዳና ላይ ተቸግረው ለሚኖሩ ወጣት ሴቶችና ህፃናት መጽሐፏን በመሸጥ ገቢ ለማሰባሰብ መሆኑን ተናግራለች።

ከአእምሮ ሕመም እንዴት እንደተፈወሰች የሚናገረው የመጽሐፉ ክፍል ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚያስተምር በመሆኑም ግለታሪኳን ለመፃፍ እንዳነሳሳት ነው የገለጸችው።

በዚህም ምክንያት የመጽሐፏን ርዕስ "የአእምሮ ፈውስ" ስትል ሰይማዋለች።

ጎዳና ላይ የሚኖሩ ሴቶችና ህፃናት ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ያለችው ፍቅርተ 5 ሴቶችን ከጎዳና ላይ አንስታ እየረዳች መሆኑን ተናግራለች።

ሁሉም የበኩሉን ቢወጣና በተለያየ መንገድ ጥረት ቢያደርግ ደግሞ ችግሩን መቀነስ ይቻላል ነው ያለችው።

ከችግሩ ስፋት አንጻር ከፍያለ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ መንግሥትና ባለሀብቶች ትኩረት ሊያደርጉበት ይገባልም ብላለች።

የአእምሮ ፈውስ መጽሐፍ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተፃፈ ሲሆን 106 ገፆች ያሉትና በአስር ምዕራፎች የተከፈለ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም