በኢትዮጵያ በዓመት የወሊድ አገልግሎት ከሚሹ ሶስት ሚሊዮን እናቶች ግማሽ ያህሉ አገልግሎቱን ያገኛሉ ጤና ሚኒስቴር

70

ጎንደር፣ ሚያዚያ 09/2013( ኢዜአ ) በኢትዮጵያ በዓመት የወሊድ አገልግሎት ከሚሹ ከሶስት ሚሊዮን በላይ እናቶች መካከል ግማሽ ያህሉ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማህበር ጋር በመተባበር በህክምና ጤና ትምህርት የሰልጣኞች እርካታ ዙሪያ ያዘጋጀው ጥናታዊ ውይይት ተካሂዷል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤናና የስርአተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በዓመት ከሶስት ሚሊዮን በላይ እናቶች የወሊድ አገልግሎት የሚሹ ናቸው፡፡

በሃገሪቱ የመንገድ አውታሮች አለመስፋፋት፣ የአንቡላንስ ተሸከርካሪዎች ቁጥር ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆንና በህብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት አገልግሎቱን ከሚያገኙ መካከል በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር 50 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምእተ ዓመቱን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ከያዘቻቸው ግቦች አንዱ የእናቶችን ሞት መቀነስ ግንባር ቀደም መሆኑን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

መንግስት የእናቶችን ሞት በመቀነስ በኩል የጤና አገልግሎትን ጥራት፣ ፍትሃዊነቱንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ባለፉት ዓመታት ሰፊ ስራዎች ሲያከናውን መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ከ100ሺ እናቶች 412ቱ በወሊድ ወቅት ለሞት እንደሚጋለጡ ጠቅሰው፤ ይህን ቁጥር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 ወደ 70 ዝቅ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማትን ማስፋፋትና ደረጃቸውን ማሻሻል እንዲሁም በዘርፉ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራትና የጤናውን ዘርፍ በዘመናዊ የጤና መረጃ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ትኩረት እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲዋይፍ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካል በበኩላቸው ከዛሬ 30 አመት በፊት የተቋቋመው ማህበሩ አላማ አንግቦ የተነሳው ሙያውን በማሳደግ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር 17 ሺህ ያህል መድረሳቸውን ጠቁመው፤ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው ሚድዋይፈሪ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ ዲን ዶክተር አስማማው አጥናፉ ኮሌጁ የሰለጠኑ አዋላጆችን በብዛትና ጥራትለማፍራት ደረጃውን የጠበቀ ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኮሌጁ የእናቶችንና የጨቅላ ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር በዘርፉ በዲፕሎማ መርሃ ግብር የጀመራቸውን ስልጠናዎች ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ማሳደግ መቻሉንም አስታውቀዋል።

ሆስፒታሉ ለወላዶች የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ በማድረግ በኩል በቂ ባለሙያዎችንና የህክምና መሳሪያዎችን አሟልቶ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘባቸው ናቸው፡፡

ሆስፒታሉ ምንም እንኳ ከፍተኛ የታካሚዎች ጫና ቢኖርበትም ለወላዶች ቅድሚያ በመስጠት አንድም እናት በወሊድ መሞት የለባትም የሚለውን የህክምና መርህ እየተገበረ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት በተለያዩ የህክምና ምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ከፌደራል ፣ክልልና ዩኒቨርሲቲው ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም