የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሳካት የአካባቢያቸውን እምቅ አቅም መጠቀም አለባቸው - የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

75

አዲስ አበባ ሚያዚያ 9/2013/ኢዜአ/ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጣቸውን ተልዕኮና የትኩረት መስክ በብቃት ለማሳካት በየአካባቢያቸው የሚገኙ እምቅ አቅሞችን መጠቀም እንዳለባቸው የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሣሙኤል ኡርቃቶ አሳሰቡ፡፡

የስምንት የምርምር እና የሁለት የሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድና የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡ 

ዩኒቨርሲቲዎቹም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በምርምር ዘርፍ ለመከወን የያዟቸውን ዕቅዶች አቅርበዋል፡፡ 

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሣሙኤል ኡርቃቶ የትኩረት መስካቸውን በምርምር ዘርፍ ያደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ምርምሮችና ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማምረት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል፡፡

በትምህርት ዘርፍ የሚታየውን የጥራት ችግር በመፍታትም የተሰጣቸውን የምርምር ግብ ስኬታማ ለማድረግ ያላቸውን አቅም መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ዘርፉ የፖሊሲ ማሻሻያ እየተተገበረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጤታማ ሊሆኑ በሚችሉበት ዘርፍ ብቻ እንዲሰሩ በመደረጉም አመርቂ ውጤት እንደሚመጣ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ምርምርን የትኩረ ዘርፍ ያደረጉ ዩኒቨርሲቲዎችም ለሚሰሩት ምርምር አካባቢያቸው ላይ ያለውን እምቅ ሃብት መመልከትና በዚህም ዙሪያ ጥናቶች መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ 

የጥናትና ምርምር ሥራዎቹ በቅድሚያ የአካባቢውን ሕዝብ ችግር የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው የገለጹት ዶክተር ሣሙኤል ከዚያም ባለፈ ለአገርና ለአህጉር እንደሚሸጋገር ገልጸዋል፡፡

ተቋማቱ አገራዊ ፋይዳን ባገናዘበ መልኩ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በምርምር ዘርፍ የተለዩት ዩኒቨርሲቲዎችም በመጪዎቹ 10 ዓመታት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቴክኖሎጂ፣ በሣይንስ፣ በአይሲቲ፣ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡ 

የሚሰሯቸው ጥናትና ምርምሮች ከአገር አልፈው በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑና ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

አዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ሐሮማያ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ጅማ እና ጎንደር የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች፤ የአዲስ አበባና የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው መለየታቸው ይታወቃል። 

በአገሪቷ የሚገኙ 46 ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት በተልዕኮና በትኩረት መስክ ተለይተው ተማሪዎች ለመቀበል በዝግጅት ላይ መሆናቸው ይታወቀል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም