በአማራ ክልል የማዕድን ዘርፍ 4 ሺህ 200 አልሚዎች ፈቃድ ወሰዱ

90

ደብረ ማርቆስ፤ ሚያዚያ 09/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል የማዕድን ሃብት ዘርፍ 4 ሺህ 200 አልሚዎች ፈቃድ ወስደው በልማቱ እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ማዕድን ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የምክክር መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ደስታየ ጥላሁን እንዳሉት፤  የማዕድን ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አሰተዋጽኦ ከሚያበረክቱት ዘርፎች አንዱና ዋነኛው ነው።

ሆኖም በክልሉ ዘርፉ ከዚህ በፊት ትኩረት ተነፍጎት የቆየና ትልልቅ የማዕድን አልሚ ባለሃብቶች ጭምር  ሳይሳተፉበት መቆየቱን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ያለውን እምቅ የማዕድን ሃብት አልምቶ ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን እንዲወጣ ለማስቻል በተደረገ እንቅስቃሴ 4 ሺህ 200 አልሚዎች ፈቃድ ወስደው በልማቱ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ስራ በገቡ ማዕድን አልሚዎችም  ለ32 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ብቻ ከ"ሮያሊት " ክፍያ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውቀዋል።

ይህም ሆኖ አሁንም በገቡት ውል ልክ ወደ ልማት ያልገቡና ቦታውን አጥረው ያስቀመጡ እንዳሉ ጠቅሰው፤ ደካማ አፈፃፀም ያላቸውን በመለየትም ፈቃድ የመሰረዝና ለአዳዲስ አልሚዎች የመስጠት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ለግንባታ ፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢነርጂ፣ ጌጣጌጥና መሰል አገልግሎት የሚውሉ በርካታ የማዕድን ሃብት በመኖራቸው በአግባቡ ለምቶ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆንም በተደራጀ አግባብ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

ላሊበላ ጅብሰም እና የግንባታ እቃዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጣእም ያለው ወተት በበኩላቸው ፤ የማዕድን ዘርፉ ቀጣይ እድገት እንደሚዘገብ ተገቢው ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዘርፉ እድገት የሚያግዙና ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችም ለአምራቾች በቀላሉ የሚያገኙበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በ"ግራናይት" ማዕድን ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አቶ እናውጋው መላኩ በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎች ተገቢውን እገዛ ማድረግና የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር፥ ምዕራብ እና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች በማእድን ልማት የተሰማሩ አካላትና አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም