በአረጋዊያን መርጃ ማዕከላት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ እርምጃዎች በአግባቡ ሊተገበሩ ይገባል

74

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 9 /2013 (ኢዜአ) በአረጋዊያን መርጃ ማዕከላት የኮቪድ-19 ወረርሽኘን ለመከላከል የተቀመጡ የጥንቃቄ ተግባራት በአግባቡ ሊተገበሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማዕከል ለሚገኙ 97 አረጋዊያን የኮሮናቫይረስ ክትባት ተሰጥቷል።

ለአረጋዊያኑ ክትባቱን የሰጠው የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ነው።      

ሆስፒታሉ ከሦስት ዓመት በፊት ከማዕከሉ ጋር በገባው ስምምነት መሰረት በማዕከሉ ለሚገኙ አረጋዊያን የሕክምና ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።   

የዛሬው ክትባትም የዚሁ ስምምነት አካል እንደሆነ ነው የተገለጸው።  

የሆስፒታሉ ሐኪም ዶክተር ዘላለም ይርጋ እንዳሉት፤ ስለ ክትባቱ ጥቅም ቀደም ሲል ግንዛቤ በመፈጠሩ አረጋዊያኑ ያለምንም ችግር ክትባቱን ወስደዋል።    

"ክትባቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያግዛል" ያሉት ዶክተር ዘላለም በማዕከሉ በዕድሜ የገፉና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ስለሚገኙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኅብረተሰቡ የሚያሳየው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው፤ የእጅ ንጽህና በመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግና ርቀትን በመጠበቅ ራስንና ሌሎችን መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።   

የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማኅበር ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ገብረሥላሴም የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሰረት ማንኛውም ጎብኚ ወደ ማዕከሉ እንዳይገባ መደረጉን ገልጸዋል።  

በማዕከሉ አረጋዊያንን የሚንከባከቡ ሠራተኞች ከግቢው እንዳይወጡ በማድረግ በተወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ እስካሁን በማዕከሉ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው አለመኖሩን ተናግረዋል።   

እንደ አቶ ግርማ ገለጻ ክትባቱን በቅድሚያ አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች እንዲወስዱ የተደረገ ሲሆን 'በዛሬው ዕለትም ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆነና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ተከትበዋል' ብለዋል።

ማዕከሉ በቀጣይም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ያልተከተቡ አረጋዊያን ክትባት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት መሰጠት ከጀመረ አንስቶ እስካሁን ድረስ ከ430 ሺህ በላይ ዜጎች መከተባቸውን ጤና ሚኒስቴር ትናንት ይፋ አደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም