ኤጀንሲው ያሳካቸው ውጤቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት ማሳያ ናቸው -ጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ

110

ሚያዚያ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) "የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ያሳካቸው ውጤቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት ማሳያ ናቸው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን አዲስ ሕንጻ ሲመርቁ ነው።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሐሳብ ሲጠነሰስ በርካቶች እንደ እብደት በመቁጠር በኢትዮጵያ የማይሳካ አድርገው ሲያስቡት እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን ተቋሙ በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ዛሬ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን የሚበቃ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ "የኢትዮጵያ ብልጽግና ለብዙዎች ሕልም ቢመስልም የሚሆንና ትውልዱ የሚመለከተው እውነት ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ የሚያስቆም ምንም አይነት ኃይል እንደሌለም አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ወሎ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተገነባው የተቋሙ ሕንጻ ባለ 14 እና ባለ 17 ወለል የሆኑ አምስት ሕንጻዎችን ያካተተ ነው፡፡

የሕንጻው ግንባታ በ2002 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን 2 ቢሊዮን 142 ሚሊዮን 58 ሺህ 790 ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ኤጀንሲው ላለፉት 13 ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች በተከራያቸው ሕንጻዎች ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።

በየዓመቱም ለሕንጻ ኪራይ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርግ ነበር።

የሕንጻው መገንባት ለኪራይ የሚወጣውን ወጪ ከማስቀረቱም በላይ ከቦታ ወደቦታ በሚደረግ እንቅስቃሴ ይወድም የነበረውን የተቋሙን ንብረት መታደጉን አንስተዋል።

ዶክተር ሹመቴ ዓለም ከአካላዊነት ወደ ዲጅታል እየተቀየረች ባለችበት በዚህ ወቅት የሳይበር ጉዳይ ፋታ የማይሰጥ ስራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ጦርነቶች ከመሬት ላይ አውደ ውጊያ ወደ ሳይበር ዞረዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አንጻር ኤጀንሲው የትኛውንም ጥቃት ለመመከትና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መልሶ ለማጥቃት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቀድሞው የኤጀንሲው ዳይሬክተርና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት እንዲገነባ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።

የሠላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የሕንጻው ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስራዎች በፍጥነት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የኤጀንሲውን ሃሰብ ከመጠንሰስ ጀምሮ እውን እስኪሆን ያበረከቱትን አስተዋጽኦ "እጅግ የሚደነቅ" ሲሉም አመስግነዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና መስሪያ ቤት ርዕደ መሬትን እንዲቋቋም ተደርጎ የተገነባ ሲሆን በውስጡም እጅግ ዘመናዊ ተክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ነው።

በሕንጻዎቹ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲን ጨምሮ የሠላም ሚኒስቴር፣ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከልና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል የሚገለገሉባቸው ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም