ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዓውደ ርዕይን ጎበኙ

99

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዓውደ ጥናትና ዓውደ ርዕይን ጎብኝተዋል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የተከፈተውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ዓውደ ጥናትና ዓውደ ርዕይ ዛሬም ቀጥሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዓውደ ርዕዩ ላይ ተገኝተው የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ስራዎችን ጎብኝተዋል።

አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ የሰው ልጅ በተፈጥሮና በሕይወት ዑደት የሚያገኛቸውን የማሰብ፣ የመገንዘብ የማመዛዘን፣ የማቀድ፣ ምክንያታዊ የመሆን፣ የመማርና በቋንቋ የመግባባት ክህሎቶችን በረቀቀ ቀመር ማሽኖችን በማስተማር የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

የማዕከሉ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ዘውዴ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በፋይናንስ፣ በትራንስፖርት፣ በሚቲዎሮሎጂ፣ በኤሮስፔስ እና ሌሎች ዘርፎች ገቢራዊ ለማድረግ ስራውን ጀምራለች ብለዋል።

የዐውደ ርዕዩ ዓላማም የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂን ምንነት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

በአውደ ርዕዩ የተሳተፉ ድርጅቶችና ተቋማት መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑንና ለግሉ ዘርፍ የሚደረገው ድጋፍ ከተጠናከረ ሌሎች አገራት በዘርፉ የደረሱበት ደረጃ መድረስ እንደሚቻል ገልፀዋል።

በፋይናንስ ዘርፍ አዲስ አገር በቀል ቴክኖሎጂ ይዘው የቀረቡትና ከ'ቻፓ ፋይናንሺያል ቴክኖሎጂ' የመጡት አቶ እስራኤል ሞገስ “አውደ ርዕዩ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ጉልህ ፋይዳ አለው” ብለዋል።

ራሱን በራሱ የሚያሽከረክር መኪና ሞዴል ይዛ የቀረበችው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ኢጲሳም አብዱላሂም መንግስት ለዘርፉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠይቃለች።

ማዕከሉ አገር አቀፍ የምርምርና ልማት ማዕከል በማቋቋምና የመለኪያ መስፈርቶችን በማዘጋጀት የዲጂታል ዳታ ክምችትን በጥራት እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም