በጋሞና ሀድያ ዞኖች በመስኖ ከለማ መሬት ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኘ

108

አርባ ምንጭ/ሃዲያ፤ ሚያዝያ 09/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጋሞና ሀዲያ ዞኖች በዘንድሮ የበጋ ወቅት በባህላዊና ዘመናዊ መስኖ ከለማ መሬት ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱ ተገለጸ።

የጋሞ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የአነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ ስንታሁ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በወቅቱ  86 ሺህ 623 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት ተችሏል።

ይህም ከእቅዱ ከ2ሺህ ሄክታር በላይ  ብልጫ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

በዞኑ 14ቱም ወረዳዎች የእጅ ውሃ ጉድጓዶችን፣ የጎለበቱ ምንጮችን፣ ጅረቶችንና 1 ሺህ 545 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች በመጠቀም ልማቱ መካሄዱን ጠቅሰዋል።

ባህላዊና ዘመናዊ የመስኖ ልማቱ የተካሄደው በዋናነት ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይ ስር፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቆስጣና ሰላጣ መሆኑን ጠቁመው ከዚህም 4 ሚሊዮን 325 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

በልማቱ ከ13 ሺህ የሚበልጡ ሴቶችን ጨምሮ 224 ሺህ 494 አርሶ  አደሮች መሳተፋቸውን  ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የተገኘው ምርት ካለፈው ዓመት ብልጫ እንዳለው ጠቁመው  በተለይ ዘንድሮ የተሻለ የውሀ አማራጭ መኖሩ፣ የአርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ግብአት  አጠቃቀም ልምድ መጎልበት አበላጫ ምርት  እንዲገኝ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዞኑ ምዕራብ  ዓባያ ወረዳ የዋጅፎ ቀበሌ  የልማት ጣቢያ  ባለሙያ አቶ ዓለሙ ቶማ በሰጡት አስተያየት፤ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ማሰባሰብ  ድረስ ለአርሶ  አደሩ በቅርበት የሙያ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የቀበሌው የልማት ስራ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው አስችሏል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቀበሌው በመስኖ የለማው ምርት ሙሉ በሙሉ በመሰብሰቡ  አርሶ አደሩ ማሳውን ለበልግ እርሻ እያዘጋጀ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በወረዳው የፉራ ቀበሌ ሞዴል አርሶ አደር ማቴዎስ ማንቺካ በበኩላቸው የመስኖ ውሃ በመጠቀም ሶስት ሄክታር ይዞታቸው ላይ ቲማቲም በማልማት ምርታቸውን ለገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር አለማየሁ አምቡርቀ በበኩላቸው በበጋ መስኖ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ሽንኩርት መሰብሰብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ያጋጠማቸው የጀነሬተር ቢንዚንና የሰብል በሽታ መከላከያ መድሀኒት እጥረት በመስተካከሉ በልማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

የደላላ ጣልቃ ገብነት ደንቃራ ካልሆነባቸው በቀር ከምርት ሽያጩ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በሀድያ ዞን በመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት ስራ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖና አግሮኖሚ ባለሙያ ወይዘሮ አባይነሽ አባተ  ገልጸዋል።

ምርቱ የተገኘው በዞኑ በባህላዊና ዘመናዊ  በመስኖ ከለማው 34 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።

የተገኘው ምርት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር  በስምንት በመቶ ኩንታል ብልጫ ማሳየቱን  ተናግረዋል።

ለመስኖ ልማቱ ከ340 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና 64 ሺህ ኩንታል የአትክልትና ጥራጥሬ ሰብል ዓይነቶች ምርጥ ዘር እንዲሁም የአረምና የሰብል በሽታ መከላከያ ኬሚካል ቀርቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቅሰዋል።

በዚሁ ከጥቅምት ወር ወዲህ በተካሄደው የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ 101 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

በምዕራብ ሶሮ ወረዳ የአርጫ ቀበሌ አርሶ  አደር ከበደ መጊሶ በሰጡት አስተያየት፤በመጀመሪያው ዙር ባላቸው ሁለት  ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት በቆሎ እስካሁን ከ45 ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

በባህላዊ የመስኖ ስራን ማከናወን ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ያስታወሱት አርሶ አደሩ ከአካባቢው ጋር ተስማሚነት ያላቸው  አዝዕርቶችን በማልማት በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ወርቄ ዶበባሞ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ከሚገኝ ወንዝ ውሃ በመጥለፍ በ1 ነጥብ 5 ሄክታር ይዞታቸው ላይ ካለሙት ድንች 75 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 በየዓመቱ ከሚያካሂዱት የመስኖ ልማት እስከ 50 ሺህ ብር ትርፍ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የጊዳቻሞ ቀበሌ አርሶ አደር አየለ ሂቤቦ ናቸው።

በተለይ በመስኖ የማለማው የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ብዙ ልፋት የማይጠቅና የቤተሰብን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት አርሶ አደሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም