የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ሻምፒዮና ነገ ፍጻሜውን ያገኛል

61

መጋቢት 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) በድሬዳዋ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 13ኛው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ሻምፒዮና ነገ ይጠናቀቃል።

ከሚያዚያ 2 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ሻምፒዮና በወንዶች ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሲዳማና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋና አዲስ አበባ አስተዳደሮች ተሳትፈዋል።

በሴቶች ኦሮሚያና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም የድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

ዛሬ በሴቶች በተካሄደ ጨዋታ አዲስ አበባ ድሬዳዋን 30 ለ 17 በማሸነፍና በውደድሩ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።

ኦሮሚያ በአራት ነጥብ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ በሁለት ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በወንዶች ትናንት በተካሄዱ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ኦሮሚያ ሐረሪን 35 ለ 17 እንዲሁም ጋምቤላ ሶማሌን 33 ለ 24 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፈዋል።

አሸናፊዎቹ ጋምቤላና ኦሮሚያ ነገ በፍጻሜ ውድድሩ የሚፋለሙ ሲሆን ሐረሪና ሶማሌ ለሶስተኛ ደረጃ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ የዘንድሮው የእጅ ኳስ ሻምፒዮና ከ2007 ዓ.ም በኋላ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የጸጥታ ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሻምፒዮናው ላለፉት ስድስት ዓመታት ሳይካሄድ መቅረቱን ተናግረዋል።

“ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ሻምፒዮናው ሳይቆራረጥ በየዓመቱ እንዲካሄድ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ይሰራል” ብለዋል።

12ኛው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ሻምፒዮና በ2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተናጋጅነት መከናወኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም