"የሠላም ሩጫ ለሠላማዊ ምርጫ" የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"የሠላም ሩጫ ለሠላማዊ ምርጫ" የአምስት ኪሎ ሜትር ውድድር ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8 /2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ "የሠላም ሩጫ ለሠላማዊ ምርጫ" በሚል መሪ ሀሳብ የአምስት ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ሚያዚያ 17 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለፀ።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ወጣቶች የሠላም በጎ ፈቃደኛ ማህበር ከወጣቶችና ስፖርት አመራሮች ጋር የውድድር ዝግጅቱን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል።
የመዲናዋ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳዊት ትርፉ የአገር ዘላቂ ሠላም ሲረጋገጥ ቅድሚያ ተጠቃሚዎቹ ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
"በአገሪቷ ሠላም እንዳይሰፍን የሚሰሩ ሃይሎች አሉ" ያሉት አቶ ዳዊት፤ ወጣቶች ይህን በመረዳት አንድነትና አብሮነትን ከሚሸረሽሩ አስተሳሰቦች መውጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይ ለሠላም መረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የስፖርቱ ማኅበረሰብ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ስፖርት ለሠላምና ወንድማማችነት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ተከትሎ የነበረው የሕዝቡ የአንድነት ስሜት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች የሠላም በጎ ፈቃደኛ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ጣሰው በበኩሉ የሠላም እጦት በዜጎች ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ቀውስ የከፋ መሆኑን ገልጿል።
የስፖርት ቤተሰቡ ስፖርት ለሠላምና ለአገራዊ አንድነት ያለውን ፋይዳ በመረዳት ሳይታክት መስራት እንዳለበትም አመልክቷል።
የሩጫ ውድድሩ የኮቪድ-19 መከላከል መመሪያን በመተግበር በ11ዱ ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ቦታዎች እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።