ግብጽ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ጉዳት እንደማያደርስባት ገለጸች

85

ሚያዚያ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ትላንት ለሀገሪቱ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ግብጽን አይጎዳትም ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በመጪው ሀምሌ ወር ለመሙላት ማቀዷ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የውሃ ሙሌቱ ግብጽን እንደማይጎዳት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች።

ዘ ናሽናል ኒውስ በድረ ገጹ እንዳስነበበው ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በግብጽ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ እንደሌለ ገልጸው ሊፈጠር የሚችል ተጽእኖ ካለም ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

"ይህንን ማብራሪያ የምሰጣችሁ በባለሙያዎች የተሰሩ የቴክኒክ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ በሚመጣው ክረምት በኢትዮጵያ ከተለመደው በላይ ዝናብና ጎርፍ የሚጠበቅ በመሆኑ ግድቡ ቢሞላ ግብጽ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንደሌለው ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አያይዘውም ጎርፉ የአስዋን ግድብ ለመሙላት ተጨማሪ ውሃ የመስጠት እድል አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት በግብጽም ይሁን ሱዳን ላይ ጉዳት እንደማያስከትል በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

በመጪው የክረምት ወራት ውስጥ የሚከናወነው የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት እንዲቻል ሁለቱ ሀገራት ባለሙያዎቻቸውን እንዲልኩ ጥሪ መቅረቡም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም