ሴራ ያልበገረው የኢትዮጵያውያን ህብር

100

አብዱራህማን ናስር /ኢዜአ/

በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ስለሚቀጥልበት ሁኔታ ለመነጋገር የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች ከመጋቢት 25-28 ቀን 2013 ዓ.ም በኮንጎ ኪንሻሳ ስብሰባ አካሂደው ነበር። ስብሰባው በኮቪድ ምክንያት ለረጅም ጊዜያት በአካል ሳይገናኙ ከቆዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደ ነው። የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼኬሴዲ በየካቲት ወር 2013 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነትን ቦታ ከተረከቡ በኋላ ያካሄዱት የመጀመሪያ መድረክም ነው።

የኪንሻሳው መድረክ ሶስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የየሀገራቸውን አቋም ያቀረቡበት ነበር። የኢትዮጵያን አቋም አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ንግግር የአባይ ውሃ ጥቅም ላይ የሚውለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መሆኑን አብራርተዋል። አያይዘውም የህዳሴው ግድብ ለኢትየጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አጠቃላይ የጋራ የልማት ዕድል የሚከፍትና ትብብርን ማእከል ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ከምንም ቅድመ ሁኔታ ጋር እንደማይገናኝ ይልቁንም በዚህ ዙሪያ አስፈላጊ መረጃና ዳታ በጋራ ለመለዋወጥ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። ድርድሩ በትብብርና ሁሉም አሸናፊ ሊሆን በሚያስችል ሃሳቦች ላይ መሰረት በማድረግ መካሄድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በየጊዜው ተለዋዋጭ ሀሳብ ይዘው የሚቀርቡት ግብጽ እና ሱዳን እንደተለመደው ሁሉ አዳዲስ ሃሳቦችን ይዘው ነበር የቀረቡት። ሁለቱ ሀገራት ከሚግባቡባቸው ይልቅ የሚለያዩባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ለጊዜውም ቢሆን የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት እንዲጣመሩ አድርጓቸዋል። ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሃሳብ በመደገፍና አጽንኦት በመስጠት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ የግድቡ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት “እኛ ሳንፈቅድ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት አትችሉም” በማለት የአልሞት ባይ ተጋዳይ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ። 

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንደሚያመለክተው በኪንሻሳው መድረክ በሁለቱ ሀገራት ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል የድርድሩ ፎርማት እንዲቀየርና ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተመድ እኩል ሚና እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ የናይልን ወንዝ 85 በመቶ ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት ላይ አስገዳጅ ውል ሳይፈረም የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መከናወን የለበትም የሚል አቋም ይዘው ቀርበዋል። በግድቡ የውሃ ሙሌት ምክንያት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ለከፍተኛ የውሃ እጥረት አደጋ መጋለጣቸውንም አቅርበዋል።

ግብጽ እና ሱዳን ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣና በሌሎች አደራዳሪዎች እንዲጀመር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ በዋናነት የምታቀነቅነው ግብጽ ብትሆንም መነሻ ሃሳቡን በሱዳን በኩል ቀርቦ የጋራ አቋማቸው መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገራት “የአፍሪካ ህብረት ችግሩን መፍታት አልቻለም” በሚል ጉዳዩን በነፃነት ለመምራት እንዳይችል እና የተሰጠውን ሃላፊነት በሚያኮስስ መልኩ ሌሎች ተዋናዮች  አብረው እንዲመሩ ግፊት ሲያደርጉም ቆይተዋል።

ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣና በሌሎች አካላት እንዲታይ ድጋፍ ለማግኘት የግብጽ ባለስልጣናት በርካታ ሀገራትን ዞረዋል። ይሁን እንጂ እንደ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሶስቱ ሀገራት እኩል ተጠቃሚ በሚያደርግ መርህ መሰረት ውይይቱ እንዲቀጥል ምክረ ሃሳብ ከመስጠት በስተቀር የግብጽን ዓላማ የሚደግፍ የተለየ አቋም አላሳዩም። ግብጽ እና ሱዳን ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት እንዲወጣ ግፊት የሚያደርጉበት ምክንያት የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከመከናወኑ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ እንዲበረታና የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት ነው።    

የኢፌዴሪ የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጀነር ስለሺ በቀለ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ግብጽና ሱዳን የያዙት አቋም የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብ እና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያጸና አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ግፊት ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ሁለቱ ሀገራት በግድቡ የውሃ ሙሌት ምክንያት ህዝባችን ለአደጋ ተጋልጧል በሚል የሚያቀርቡት ክርክር ፍጹም የተሳሳተ መሆኑንም አስምረውበታል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በተከናወነበት ባለፈው ክረምት በየቀኑ 90 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ከግድቡ በታችኛው ውሃ ማስወጫ እየፈሰሰ እንደነበር አብራርተዋል። ግድቡ ከሞላ በኋላ ደግሞ ሞልቶ የሚፈሰውም ጭምር ሲደርሳቸው እንደነበር በማስታወስ ሱዳን በወቅቱ የውሃ እጥረት ሳይሆን ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ አጋጥሟት እንደነበር ጭምር ገልጸዋል።

ከግድብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የረጅም ዓመታት ልምድ እንዳላቸው የሚነገረው የቀድሞው የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትር ዶ/ር ኡስማን አቱም ሰሞኑን ከስካይ ኒውስ አረቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በሁለተኛውም ይሁን በሦስተኛው ዙር በሱዳንና ግብጽ ላይ ምንም አይነት ጉዳትና አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማይኖረው አብራርተዋል፡፡ ግድቡ የታቀደለትን የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ መካከለኛ የፍሰት መጠን የሚባለውን 48 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ ታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገሮች መልቀቅ እንደሚችልም አክለው ገልጸዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ጉዳት ያስከትላል በሚል የሚጠቀሱ ችግሮች በአብዛኛው የተሳሳቱ መሆናቸውን ዶ/ር ኡስማን ተናግረዋል።

የህዳሴው ግድብ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ተጽእኖ እንደማያሳድር እውነታው በተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎች የተነገረ ቢሆንም ግብጽ እና ሱዳን ሁለተኛው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት “እኛ ሳንፈቅድ” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ ማሰማት ተያይዘውታል። የግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲ ሲ ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን ያስተላለፉት መልእክት የበርካታ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ ነበር። ፕሬዝዳንቱ "ማንም ከግብጽ ውሃ ላይ አንዲት ጠብታ መውሰድ አይችልም፤ ቀይ መስመር ነው፤ ይህ ከሆነ ደግሞ በቀጠናው አካባቢ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ አለመረጋጋት ይፈጠራል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በምንም መልኩ የግብጽን ጥቅም የሚነካ ከሆነ ጠንካራ እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል። አንዳንድ ፖለቲከኞቻቸውም የግድቡ የውሃ ሙሌት ከ80 ቀናት በታች የቀሩት በመሆኑ ግብጽ ጊዜ ሳትወስድ ለጦርነት መዘጋጀት አለባት በማለት መናገር ጀምረዋል።     

በሱዳን በኩል የጦርነት አማራጭ ተቀባይነት እንደሌለው ባለስልጣኖቻቸው እየገለጹ ቢሆንም በግብጽ በኩል ግፊትና ጫና እየበረታባቸው እንደሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርያም አል ሳድቅ ከኪንሻሳው መድረክ በኋላ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ? በሚል ከመገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በፍጹም ወታደራዊ አማራጭ ቦታ የለዉም፤ መፍትሄ ሊሆንም አይችልም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ግብጽ ዓላማዋን ለማሳካት ሱዳንን ለማግባባት እየሰራች ሲሆን ለዚህም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ወደ ካይሮና ካርቱም በመመላለስ በርካታ ውይይቶችን አካሂደዋል። በቅርቡ ሁለቱ ሀገራት የጋራ ወታደራዊ የጦር ልምምድ እስከማድረግ የደረሰ ትእይንት አሳይተዋል፤ የጋራ ስምምነትም ተፈራርመዋል።

የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ሱዳንን እንደማይጎዳ፤ ይልቁንም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚሰጣቸው የራሳቸው ምሁራን ያረጋገጡት እውነታ ነው። የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትሩ ዶ/ር ያሲር አባስ ከዓመት በፊት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ግድቡ ከኢትዮጵያ ይልቅ ሱዳንን እጅግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነበር። የግድቡን አሰራር በተመከለተም ከዘመናዊ ግድቦች በተሻለ መልኩ ከፍተኛ ሙያ ባላቸው መሀንዲሶች የተሰራ መሆኑን በመጠቆም ምንም ዓይነት የቴክኒክ ችግር እንደሌለበት ነበር የገለጹት። ሚኒስትሩ አሁን አቋማቸውን ቀይረው ግብፅ የምታራምደውን ሃሳብ በመደገፍና በማስፈጸም ላይ መሆናቸው ሁለት ቦታ እየረገጡ ነው በማለት ብዙዎች በትዝብት ይናገራሉ።

ግብጽ የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ እውን መሆኑ እንቅልፍ ከነሳት ውሎ አድሯል። አልተሳካላትም እንጂ ግድቡ ውሃ ከመያዙ በፊት ለማውደም እቅድ እንደነበራት በተለያዩ ጊዜያት ያደረገቻቸው ሙከራዎች ያስረዳሉ። በፈረንጆቹ 2013 ሰኔ ወር የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ ከሀገሪቱ ፖለቲከኞች ጋር በመሆን በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ዝግ ስብሰባ አድርገው ነበር። የዚህ ስብሰባ ዋና ዓላማ የህዳሴው ግድብ እንዴት ማደናቀፍ እንደሚቻል ስትራቴጂዎችን መንደፍ ነበር።

በውይይቱ ግድቡን ከማፍረስ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት እርስ በርስ ግጭት መፍጠር እንደሚቻል የቀረበበት ሲሆን ሳይታወቅ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ስርጭት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማድረሱ ገመናቸው እንዲጋለጥ በር ከፍቷል። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን “የግብጽ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም በሚስጢር የተነጋገሩት ይፋ ወጣ” በማለት ነበር ተቀባብለው የዘገቡት። በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ጽንፈኛ አቋም ካላቸው ተቃዋሚዎች ጋር ልዩ ግንኙነት በመፍጠርና በመደራደር የግድቡን ግንባታ ማስተጓጎል እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ የተወሰደ ነበር።

ሌላኛው ስትራቴጂ የህዳሴው ግድብ ላይ ግብጽ የአየር ጥቃት ልትፈጽም እንደተዘጋጀት በማስመሰል ሽብር የሚፈጥሩ ወሬዎችን በማናፈስ በህዝቡ ላይ ስጋት እንዲፈጠር ማድረግ የሚል ነበር። ይህ ሁሉ ተደርጎ ውጤት ካላመጣ የመጨረሻው አማራጭ ግድቡን ማፍረስ ነው ብለዋል። የህዳሴው ግድብ አሁን ቀጥታ ማፍረስ የማይቻልበት ደረጃ በመድረሱ የማይሞከር ቢሆንም ፕሮፖጋንዳዎቹ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች የስትራቴጂው አካል መሆኑን መዘንጋት አይገባም። 

የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ በአባይ ላይ የሚከናወን የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ አጥብቃ ስትቃወም ዓመታትን አስቆጥራለች። የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት እንዳይጀመር፤ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶችን አድርጋለች። ግብጽ ግድቡ በሚገኝበት ስፍራ ቢሮ በማቋቋም ግድቡን ለማስተዳደርና አጠቃላይ እንቅስቃሴውን ለመቆጣጠር ጥያቄ እስከማቅረብም ደርሳ ነበር። በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ መልእክት የሚያስተላልፉ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችንም ከፍታ እየሰራች መሆኑን በቅርቡ ፌስ ቡክ የዘጋቸው ገጾች ማሳያ ናቸው። እንደ ቢቢሲ ዘገባ እነዚህ የፌስ ቡክ አካውንቶች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ 525 ሺህ ዶላር ወይም 21 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወጪ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት የምታከናውነው ከራሷ ከሚመነጭ ውሃ እንጂ ከሌላ ሀገር ወስዳ አይደለም። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የውሃ ሙሌቱ ከታቀደለት መርሃ ግብር አንድ ዓመት በዘገየ ቁጥር በግንባታ መጓተት እና በቀጥታ ከሚገኘው ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ በቀጥታ ያሳጣል። ስለሆነም በግብጽና ሱዳን በኩል የውሃ ሙሌቱን ሂደት ለማስተጓጎል የሚደረግ ማንኛውም የሴራ እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ኢትዮጵያ አጽንኦት የሰጠችው ጉዳይ ነው።  

የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኢትየጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተሳሰረ፣ ሁሉም በአንድ ላይ የህብር ዜማ እንዲያዜሙ ያደረገ የሀገሪቱ የከፍታ ምልክት ነው። ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳ ልዩነቶች ቢኖሯቸውም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ አይደራደሩም። የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባሳለፍነው ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም በስኬት ሲከናወን ህዝቡ ደስታውን እንደገለጸው ሁሉ በመጪው ክረምት የሁለተኛው ዙር ሙሌት በስኬት ተከናውኖ የላቀ ደስታውን ለመግለጽ ዝግጅት ላይ ነው።

ቸር እንሰንብት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም