ብልጽግና ፓርቲ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ የስነ ምግባር ስልጠና እየሰጠ ነው

89

ነገሌ ፤ ሚያዚያ 07/2013 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በጉጂ ዞን ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሀዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማገዝ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ የስነ ምግባር ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገለጸ፡፡

በፓርቲው ጽህፈት ቤት የጉጂ ዞን  ሀላፊ አቶ በገጃ ሞርጌ እንዳሉት፤  ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት   በዞኑ ለሚገኙ 131 ሺህ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ነው።

የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ብልጽግና ፓርቲ ከማዕከል እስከ ዞን በምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ላይ አትኩሮ እየሰራ መሆኑንም  ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው ቀደም ሲል ዓላማዎቹን፣ ፕሮግራሞቹንና ፖሊሲዎቹን ለህዝብ ይፋ አድርጓል፣ አሁን ደግሞ የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ስልጠና እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫውን ቢያሸንፉ በአምስት ዓመታት የስልጣን ዘመን የሚሰራቸውን የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅዶች ለህዝብ በማቅረብ የምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ከጉጂ ዞን የተሻለ እውቀትና ልምድ ያላቸው  ለህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ 16 ዕጩዎች ማቅረባቸውንና ከመካከላቸውም ስድስቱ ሴቶች መሆናቸውን ሀላፊው አስታውቀዋል፡፡

ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ ቅድሚያ ሀገር ሰላም መሆን ስላለበት ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የጉጂ ዞን ህዝብ ሰላሙን በንቃት እንዲጠብቅና በምርጫው  ተሳትፎ በማድረግ ድምጹን ለብልጽግና ፓርቲ እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም