መገናኛ ብዙሃን ትውልድ ለመቅረፅ ጉልህ ሚና ላላቸው አረጋዊያን ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

92

ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) ያልተበረዘ የታሪክና የእውቀት የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር የአረጋዊያን ሚና ከፍያለ ቢሆንም መገናኛ ብዙሃን ለእነርሱ የሚሰጡት ሽፋን ዝቅተኛ መሆኑ ተገለጸ።

ታሪክና ባሕል ደርዝ ይዞ እንዲቀጥል፣ አገራዊ ዕውቀት ለትውልድ እንዲተላለፍ፤ መልካም አስተሳሰቦችን በማራመድና ትውልድ በመቅረጽ የአረጋዊያን ሚና ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የላቀ ነው።

የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበርና ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል አረጋዊያንን ያካተተ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን መሆን አለበት ሲሉ በጋራ መክረዋል።

የሚኒስቴሩ የአረጋዊያን ጉዳይ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው አለሙ መገናኛ ብዙሃን ለአረጋዊያን እየሰጡ ያሉት ትኩረት አናሳ እንደሆነ አንስተዋል።

የአረጋዊያን የሕይወት ጉዞ፣ የታሪክና የእውቀት የትውልድ ቅብብሎሽን የማስቀጠል ሚና ትኩረት አላገኘም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ስራ እስኪያጅ አቶ እንዳሻው ታዬ በበኩላቸው  በመገናኛ ብዙሃኑ ከአረጋዊያን ይልቅ ለመዝናኛ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አረጋዊያን የሚፈለጉት ለሽምግልናና ለምርቃት ብቻ ሳይሆን የአብሮ መኖርን እሴቶች ለትውልዱ እዲያስተምሩም ሊሆን ይገባል ብለዋል አቶ እንዳሻው።

ተተኪው ትውልድ ኢትዮጵያዊ ባሕሎችና እሴቶችን ዘንግቶ መጤ ባህሎች ላይ እንዲንጠለጠል ካደረጉ ምክንያቶች አንደኛው አረጋዊያን ትኩረት መነፈጋቸው ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ጡረተኛዋ ወይዘሮ ወይንአበባ አሰፋ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃኑ ለመዝናኛ ዘርፍ ሰፊ ጊዜ በመስጠት አረጋዊያንን ትኩረት መንፈጋቸው የቆዩ እሴቶቻችንን እንድናጣ አድርጎናል ብለዋል።

ትኩረት በመነፈጋቸውም ለእነርሱ ይሰጥ የነበረው ክብር ተዘንግቷል፤ በወጣቱ ዘንድ አረጋዊያንን የማክበር ባህልም እየጠፋ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ታሪክ፣ አገራዊ እውቀት፣ ያልተበረዘ ባሕልና እሴቶች ለትውልድ እንዲተላለፉ መገናኛ ብዙሃን የአረጋዊያንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ በምክክር መድረኩ ተጠይቋል።

በኢትዮጵያ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አረጋዊያን እንደሚገኙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም