ግብጽና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ እንዲወጣ እየጣሩ ነው-- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

94

ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) ግብጽና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ከአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ እንዲወጣ እየጣሩ መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ በአበይት ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዴሞክራቲክ ኮንጎ በተካሄደው የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ኢትዮጵያ ይዛው የነበረው አቋም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ በሚል መርህ መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህን መርህ የምትከተለው አባይ በአፍሪካ አገራት የሚፈስ የአህጉሪቷ ወንዝ በመሆኑና የተፋሰሱ አገራት አፍሪካዊያን በመሆናቸው የሶስትዮሽ ድርድሩ መፍትሔም በአፍሪካ ነው ብላ ስለምታምን ነው ብለዋል።

ይሁንና ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድሩን ከአፍሪካ ሕብረት ማእቀፍ ለማውጣት አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን በመጥቀስ በኪንሻሳው ድርድር በግልጽ መታየቱን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በግድቡ የውሃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ቅድሚያ እንጋገር የሚል ሀሳብ ስታቀርብ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሙሌቱ ከመከናወኑ በፊት የአባይ ወንዝ ውሃ ድርሻና ክፍፍል ሕጋዊ ስምምነት መፈረም አለበት ሲሉ አቋማቸውን ማንጸባረቃቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይ ሱዳን በድርድሩ የሚሳተፉ ታዛቢዎች ከአፍሪካ ሕብረት እኩል ሚና ይኑራቸው በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ኢትዮጵያ ጥያቄውን አለመቀበሏን ነው አምባሳደር ዲና ያስረዱት።

ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት መፍትሔ ያገኛል ብላ እንደምታምንና በሕብረቱ ማዕቀፍ ድርድሩ እንዲቀጥል ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

በአጠቃላይ ግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍና አደራዳሪነት እንዲቀጥል ፍላጎት አላሳዩም ብለዋል።

ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ ለምታነሳቸው ጉዳዮች ኢትዮጵያ ቀደም ብላ በቂ ምላሽ በመስጠቷ በድርድሩ ላይ ቀረኝ ብላ ልታነሳው የምትችለው አጀንዳም የለም ብለዋል።

የግድቡን ደህንነት፣ የግድቡን ሙሌትና በአጠቃላይ በግድቡ ዙሪያ ሱዳን መረጃዎችን እንደምትፈልግና ኢትዮጵያ መረጃዎቹን ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ማሳወቋን ገልጸዋል።

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአገራት መሪዎች በዝግ ይካሄድ በሚል ያቀረቡትን ሃሳብ ጥናት በማድረግ ይፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥበት አመልክተዋል።

ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ አስመልክቶም ኢትዮጵያ እ.አ.አ 1972 በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው የማስታወሻ ልውውጥ ስምምነት መሰረት በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ "የሱዳንን ሕዝብ ጥቅም ከሚወክል ማንኛውም ሃይል" ጋር መስራት ትፈልጋለች ብለዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት በተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሩ ሲከፈትላቸው እያደረጉት ያለው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንጻር በተያዘው ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያና የመን 2 ሺህ 344 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።

ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት መረጃ ለመለዋዋጥ እንዲቻል ግብጽና ሱዳን ባለሙያዎችን እንዲመድቡ ያቀረበችውን ጥሪ ሁለቱ አገራት እንደማይቀበሉት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም