በጉጂ ዞን ለጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት እየተሰጠ ነው

147

ነገሌ፤ ሚያዝያ 7/2013 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን ለ3 ሺህ 991 የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የክትባት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ መስፍን ካሳዬ እንዳሉት፤ ክትባቱ በዞኑ ባሉ አራት ሆስፒታሎችና 62 ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡

እስካሁንም በነገሌ ከተማ ፣አዶላ ወዩና አጋ ዋዩ ወረዳዎች  ለ142 ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ክትባቱ በቀጣይም ዕድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎችም ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በነገሌ ሆስፒታል የተላላፊ በሽታዎች ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ቴዎድሮስ ታደሰ ክትባቱ ከራስ አልፎ እስከ ቤተሰብ ድረስ የነበረውን የስነ ልቦና ጫና ይቀንሳል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ታካሚ ሲመጣ የበሽታው ምልክት ታየበትም አልታየበት በጤና ባለሙያዎች ላይ ሲደርስ የነበረውን ስጋትና መጨናነቅን ለመቀነስ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ከቫይረሱ ተለዋዋጭ ባህሪ ጋር ተያይዞ  በክትባት ብቻ መከላከል ስለማይቻል አሁንም ቢሆን ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የጤና አገልግሎቱን ለመስጠት በራስ መተማመን ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

የተከተቡም ሆነ ያልተከተቡ ሰዎች የንጽህና መጠበቂያዎች በመጠቀም የቫይረሱን ተጋላጭነት በመከላከል ቤተሰባዊ፣ ህዝባዊና ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሆስፒታሉ የድንገተኛ ህክምና አመራር ሳሙኤል የሺጥላ በበኩላቸው ክትባቱ በውጭ እንደሚወራው ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው እስካሁን ባለው ሂደት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

በነገሌ ከተማ የንጽህና መጠበቂያዎችን የሚጠቀሙ ሰዎች ብዛት ዝቅተኛ በመሆኑ በሽታው አሁንም እንደሚያሰጋቸው ጠቁመዋል፡፡

በጉጂ ዞን ከሰኔ 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን  ከተመረመሩ 4 ሺህ ሰዎች መካከል  404 የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው  ከዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም