ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱ ገዥና ሻጭን በቀላሉ ለማገናኘት ያግዛል- የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ

5143

አዲስ አበባ ፣ሚያዚያ 7/2013 (ኢዜአ) ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱ ገዥና ሻጭን በቀላሉ ለማገናኘት፣ ወጪ ቆጣቢ የሆነ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅ የጎላ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ።

ኢትዮ-ቴሌኮም የአራተኛው ትውልድ (4ጂ) ኤል.ቲ.ኢ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎትን በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን አስጀምሯል።

ኩባንያው በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ስድስት ከተሞችን ተጠቃሚ ያደረገ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎትን ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ በይፋ አስጀምሯል፡፡

በአገልግሎቱ ወላይታ ሶዶ፣አርባ ምንጭ ፣ሆሳዕና፣ ቡታጅራ፣ ወልቂጤና ጅንካ ከተሞች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሰራ አስፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ አገልግሎቱን ሲያስጀምሩ የአራተኛው ትውልድ (4ጂ) ኤል.ቲ.ኢ.አገልግሎት በከተሞች የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣን ያደርጋል ብለዋል።

በከተሞች እየተደረጉ ያሉ የኢንተርኔት ማስፋፊያዎች የኢንተርኔት ፍሰት እንዲጨምር እያደረገ ሲሆን ዛሬ የተጀመረውም ተመሳሳይ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ተግባራዊ የተደረገባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት ከነበረው የ3ጂ ኔትወርክ አገልግሎት በ3 እጥፍ የተሻለ አጠቃቀም እንዲኖር ያግዛልም ነው ያሉት።

ስብሰባዎችን በቪዲዮ ማካሄድ ጨምሮ በኢንተርኔት በመታገዝ ስራዎችን በቀላሉ ከርቀት በማቀላጠፍ በአጠቃላይ በምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ላይ በተለይም በኮቪድ ወቅት ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል።

በከተሞች እየተደረጉ ያሉ የኢንተርኔት ማስፋፊያዎች የኢንተርኔት ፍሰት እንዲጨምር እያደረገ ሲሆን ዛሬ የተጀመረውም ተመሳሳይ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢንተርኔት ፍሰት መጨመሩ ገዥና ሻጭን በቀላሉ ማገናኘት፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ምርትና አገልግሎትን ለማስተዋወቅና የስራ እድል በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።

መሰረተ ልማቱን መዘርጋት ብቻ በቂ ባለመሆኑ የተጠቃሚዎች ዝግጁነት፣ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስችሉ ግብአቶች አቅርቦትና ሌሎች ለደንበኞች አስፈላጊ ግብአቶች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።

በአካባቢው 254 ሺህ የ3ጂ ዳታ ተጠቃሚዎች የሚገኙ ሲሆን 120 ሺህ ደንበኞች ደግሞ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎትን መጠቀም የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው አገልግሎቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴን በማሳለጥ ያለውን ፋይዳ ገልጸዋል።


በደቡብ ደቡብ ምእራብ ሪጅን ከሚገኙት 641 የሞባይል ጣቢያዎች (ስቴሽን) መካከል 67 ጣቢያዎች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ.አገልግሎት ማስፋፊያ የተደረገባቸው ናቸው።

ይህም በሪጅኑ በአጠቃላይ 610 ሺህ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ኢትዮ ቴሌኮም የአዲስ አበባ፣ የደቡብ ምስራቅ ሪጅን፣ የሰሜን ምዕራብ ሪጅን እና የምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ደንበኞቹን የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡

በተያዘው በጀት አመት 103 ከተሞች የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት እንዲኖራቸው እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የኩባንያው ደንበኞች አጠቃላይ ብዛት 53 ነጥብ 7 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን 25 ሚሊዮን ደንበኞች የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው።